የአርባ ምንጭ ሙዝ፣ የጨንቻ አፕል እና የአዊ የድንች ምርቶች በመለያ እውቅና (ብራንድነት) ተመዘገቡ

156

አዲስ አበባ ሰኔ 29 ቀን 2014(ኢዜአ) የአርባ ምንጭ ሙዝ፣ የጨንቻ አፕል እና የአዊ የድንች ምርቶች በመለያ እውቅና (ብራንድ) የተሰጣቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ዛሬ የግብርና ምርቶቹን መለያ ወይም ብራንድ ይፋ ማድረጊያ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ አካሂዷል።

በኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን አነሳሽነት በአይነታቸው የተለዩና በኀብረት ሥራ ማኅበራት አባላት የሚመረቱ የአርባ ምንጭ ሙዝ፣ የአዊ ድንች እና የጨንቻ አፕል ምርቶች አዳዲስ የብራንድ መለያና ስያሜ ተሰጥቷቸዋል ነው የተባለው።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ፤ የግብርና ምርቶች ከአገር ውስጥ አልፈው ለውጭ ገበያ አንዲቀርቡ ለማድረግ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በቀጣዩ አስር ዓመታት ተግባራዊ የሚደረጉ፤ አስር የግብርና ምርቶችን በመለየት ከአገር ውስጥ ባሻገር ለውጭ ገበያ የማቅረብ እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።

የብራንድ መለያ እና ስያሜ የተሰጣቸው የአርባ ምንጭ ሙዝ፣ የጨንቻ አፕል እና የአዊ የድንች ምርቶች የዚሁ እቅድ አካል መሆናቸውን ገልጸዋል።

የደቡብ ክልል የህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አምሪያ ሲራጅ፤ ክልሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በብዛትና በጥራት የሚመረትበት ምቹ አካባቢ መሆኑን ገልፀዋል።

በአካባቢው በስፋት ከሚመረቱት የአትክልትና ፍራፍሬ አይነቶች መካከል የአርባ ምንጭ ሙዝና የጨንቻ አፕልን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም እነዚህ ምርቶች የምርቶች በመለያ እውቅና (ብራንድ) መመዝገባቸው የምርቱን ተፈላጊነት በማሳደግና ክልሉን ለማስተዋወቅ የጎላ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል።

የአማራ ክልል የኀብረት ስራ ማሕበራት ማስፋፊያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወልደተንሳይ መኮንን፤ ምርቶቹ በልዩ ትኩረት ብራንድ እንዲዘጋጅላቸው መደረጉ ሕብረት ስራ ማሕበራቱን የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በ23 ሺህ 559 የህብረት ስራ ማህበራት ከ4 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ አባላቱ ለግብርናው እድገት ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን አንስተዋል።

በአዊ ዞን የሚመረተው የድንች ምርት በብራንድነት መመዝገቡ የምርቱን ጥራት የሚያመላክት እንደሆነም ገልፀዋል።

በክልሉ በአዊ፣ በደቡብ ጎንደር፣ በምስራቅና በምዕራብ ጎጃም ዞኖች የድንች ምርት በስፋት እንደሚመረትም ተናግረዋል።

በምርት ግብይት ማዕቀፍ ብራንድ ከመወዳደሪያ አቅም መለኪያዎች መካከል አንዱ እና አስፈላጊ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም