የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከ500 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ተዘጋጅቷል

86

ሰኔ 29/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከ500 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል መዘጋጀቱን ገለጸ፡፡

ለመርሃ ግብሩ ማስፈጸሚያ እና ለችግኞች ለሚደረገው እንክብካቤ 30 ሚሊዮን ብር በጀት መድቧል።

የባንኩ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አልሰን አሰፋ፤ የባንኩ ሰራተኞች ባለፉት ሶስት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሮች በተለያዩ አካባቢዎች ከ2 ሚሊዮን በላይ ችግኖች መተከላቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የአካባቢን ስነ-ምህዳር በማስተካከል የአካባቢ ጥበቃን በዘላቂነት ለማረጋገጠ በሚደረገው አገራዊ ርብርብ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የድርሻውን እያበረከተ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

ባንኩ ባለፉት ዓመታት በእንጦጦ እና ሌሎች አካባቢዎች አገር በቀል ችግኞችን በመትከል ለአካባቢው ስነ-ምህዳር መመለስ የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝም ነው ያነሱት፡፡

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር  በመላው አገሪቱ በሚገኙ ሰላሳ ዲስትሪክቶች  ከ500 ሺ በላይ ችግኞችን ለመትከል ቅድመ-ዝግጅት መጠናቀቁን አቶ አልሰን አመላክተዋል፡፡

የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩም በዋናው መስሪያ ቤትና በሁሉም የባንኩ ቅርንጫፎች በቀጣይ ሁለት ሳምንት ውስጥ የሚካሔድ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

ባለፉት ዓመታት ባንኩ ከተከላቸው ችግኞች አብዛኛዎቹ መጽደቃቸውን ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ ለዚህ ደግሞ በበጀት የተደገፍ እንክብካቤ ማድረግ መቻሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡

ባንኩ ለመርሃ- ግብሩ ማስፈጸሚያ እና ችግኞች ከተተከሉ በኋላ ለሚደረግላቸው እንክብካቤ ሰላሳ ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከተመሰረተ 80 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት 70 ሺህ የሚሆኑ ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞች እንዳሉት ከባንኩ የተገኙ መረጃዎች ያሳያል፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም