በክልሉ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ1ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል-የክልሉ ግብርና ቢሮ

141

ባህር ዳር፤ ሰኔ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በበጋ መስኖ ከለማው የስንዴ ሰብል ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ምርቱ የተሰበሰበው በክልሉ በበጋ መስኖ ስንዴ ከለማው 40 ሺህ ሄክታር መሬት ነው።

ለተገኘው ምርት  አርሶ አደሮች፣ የኒቨርሲቲዎችና ባለሃብቶች ከቢሮው ጋር በመቀናጀት ርብርብ በማድረጋቸው ነው ብለዋል።

በበጋ መስኖ ከለማው ስንዴ ውስጥ ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው ምርት ኮምባይነር በመጠቀም መሰብሰቡን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ምርቱ ሙሉ በሙሉ መሰብሰቡን የገለጹት አቶ ቃልኪዳን በሄክታር በአማካኝ 36 ኩንታል ምርት መገኘቱን አስታውቀዋል።

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ ከ100 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

"የተገኘውን ተሞክሮ በአግባቡ ቀምረን በመጭው የበጋ ወራት ከ150 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ዝግጅት እያደረግን ነው" ሲሉ ምክትል ሃላፊው ጠቁመዋል።

የቆጋ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ አቢዮት ብሩ በበኩላቸው በቆጋ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ዘንድሮ በተደራጀ አግባብ አርሶ አደሩ በኩታገጠም ስንዴን በማልማቱ የተሻለ ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።

በምርት ስብሰባ ወቅት የሚያጋጥመውን ብክነት ለማስቀረት በ4 ሺህ 333 ሄክታር መሬት ላይ የለማው የስንዴ ዘመናዊ የምርት ማሽን በመጠቀም መሰብሰቡን ጠቅሰው ከልማቱም ከ156 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ገልጸዋል።

ይህም መንግስት ከውጭ የሚገባውን የስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የያዘውን ግብ ለማሳካት የሚደረገውን ርብርብ ለማሳካት እንደሚያገዝ ገልጸዋል።

ለአንድ ሄክታር የሚጠጋ የእርሻ ማሳቸውን በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ አርሶ አደር ሻምበል ሞላ እና አርሶ አደር አዳሙ ቀኜ ናቸው።

በተያዘው የመኸረ ልማት ማሳቸውን በተለያዩ ሰብሎች በማልማት የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ በመጭው የበጋ ወቅትም የስንዴ ልማትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል። አርሶ አደሩ ካገኙት ምርት ውስጥ ለአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት 13 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ማልማት እንደተቻለም ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም