በንጹሐን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጉዳት በሚመለከት ለውይይት የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ምክር ቤቱ አፀደቀ

111

ሰኔ 29/2014/ኢዜአ/ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በንጹሐን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጉዳት በሚመለከት ለውይይት የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በሙሉ ድምጽ አፀደቀ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 6ኛ ልዩ ስብሰባ በወቅታዊ አገራዊ የጸጥታ ጉዳይና በንጹሃን ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ በማስመልከት የህሊና ጸሎት በማድረግ ውይይቱን አድርጓል።

በኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት የተዘራው የዘር ጥላቻ ፖለቲካ ፍሬ አፍርቶ በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን የደረሰውን ጭፍጨፋ ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ኢ ሰብዓዊ ተግባር ተፈጽሟል ተብሏል፡፡

ምክር ቤቱ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 55 ንዑስ አንቀጽ 7 በተሰጠው ስልጣን መሰረት የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶችና የአገርን ደህንነት የሚነኩ ጉዳዮች ሲከሰቱ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፡፡

በዚህም በግፍ ለተጨፈጨፉ ዜጎች የህሊና ጸሎት እንዲደረግ፣ ጉዳት ያደረሱ አካላት በህግ መጠየቅ፣ በየደረጃው ያለው የአመራር፣ የጸጥታና የፍትህ አካላት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት እንዲያስጠብቁና አጥፊዎችን ተጠያቂ እንዲያደርጉ የሚሉት በውሳኔ ሀሳቡ ተካተዋል፡፡

ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉትን ማቋቋም፣ ኢትዮጵያውያን ይሄንን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ በጋራ እንዲቆሙና በምክር ቤቱ የበላይ አመራሮች የፖለቲካ ፓርቲዎች፡ የብሔር፣ የሃይማኖት፡ የክልልና የፆታ ብዝሃነትን ታሳቢ ያደረገ ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ ምክረ ሀሳብ እንዲያቀርብ የሚሉ ናቸው፡፡

የምክር ቤት አባላት በንጹሃን ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ አስመልክቶ በተዘጋጀው የውሳኔ ሀሳብ ላይ የተለያዩ ሀሳቦችን በማቅረብ በጥልቀት ውይይት አድርገውበታል፡፡

የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ቢዘገይ እንጂ ተገቢነቱ አያጠያይቅም የሚሉት የምክር ቤቱ አባላት በቄለም ወለጋ ብሎም በሌሎች አካባቢዎች የተፈፀመው የንጹሃን ግድያና መፈናቀል የከፋ ድርጊት መሆኑን አንስተዋል።

በዚህ ደርጊት ምንም የማያውቁ ህፃናት፣ ሮጠው የማያመልጡ ሴቶችና አዛውንቶች፣ የፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸው ዜጎች በግፍ መገደላቸው ቅስም ሰባሪ መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የዜጎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት ምን እንደሆነ ከስረ መሰረቱ መታየት አለበት የሚሉት የምክር ቤቱ  አባላት፤ በዚህ ዙሪያ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ያሉ አመራሮችም በአግባቡ ሊፈተሹ ይገባል ብለዋል።

የመንግስት ትንሹ ግዴታ የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባትና ደህንነት ማረጋገጥ በመሆኑ የተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሰውን የንጹሃን ሞትና ስደት ለማስቀረት  በሃላፊነት መስራት አለበት ነው ያሉት።

የዜጎች ሞትና ስደት እንዳይፈጠር ከመጠበቅም ባለፈ ጭፍጨፋ ሲፈጸም የጸጥታ ሃይሉን ስምሪት በማዘግየት ወይም በግዴለሽነት ሃላፊነታቸውን ባልተወጡ አካላት ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ መወሰድ አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በቀጣይም በንጹሃን ዜጎች ላይ ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይደርስባቸው መንግስት አስፈላጊውን ጥበቃ በማድረግ ለህይወታቸው ዋስትና ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል፡፡

ከጥቃቱ ተርፈው ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በዱር በገደሉ ለሚሰቃዩ ዜጎች መንግስት አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ሊያቀርብ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት የውሳኔ ሀሳቡ መቅረቡ ተገቢነት ቢኖረውም ከህሊና ጸሎት ባለፈ "ብሔራዊ የሀዘን ቀን ይታወጅ" የሚል ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡

በንጹሃን ዜጎች ላይ የተደረገውን ጭፍጨፋ በማንና እንዴት እየተፈጸመ እንደሆነ ለመረዳት ኢትዮጵያ ያለችበትን ጂኦ ፖለቲካ በሚገባ ማወቅ ይገባልም ብለዋል፡፡

አሸባሪው ሸኔ በንጹሃን ላይ ጥቃት የሚያደርሰው ከውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶች የተሰጠውን አገር የማፍረስ ተልዕኮ ለመፈጸም እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

  

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ  ታገሰ ጫፎ፤ በውሳኔ ሀሳቡ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች ከህጎችና መመሪያዎች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸው ታይቶ እንዲካተቱ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ በውሳኔ ሃሳቡ መሰረት የሚመረጡ የኮሚቴው አባላት የተለያየ ሀይማኖት፣ ብሔርና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተ ይሆናል ብለዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በጉዳዩ ላይ በስፋት ከተወያዩ በኋላ የውሳኔ ሃሳብ ቁጥር 10/2014 ሆኖ በአብላጫ ድምጽ አጽድቀውታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም