ህጻናት አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያገኙና ንቁ ሆነው እንዲያድጉ የህጻናት ማቆያ ማዕከላትን ተደራሽ ማድረግ ይገባል

254

ሰኔ 28/2014 (ኢዜአ) የነገ አገር ተረካቢ የሆኑ ህጻናት አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያገኙና ንቁ ሆነው እንዲያድጉ የህጻናት ማቆያ ማዕከላትን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አዲስ አበባ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ገለጸ፡፡

ቢሮው በሁሉም ክፍለከተሞች ሞዴል የህጻናት ማቆያ ማእከላት እንዲቋቋሙ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ መሆኑም አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በዛሬው ዕለት ሁለት የህጻናት ማቆያ ማዕከላትን ያስመረቀ ሲሆን  የአፍሪካ ህጻናት ቀን የማጠቃለያ ፌስቲቫልን አስመልክቶም መግለጫ ሰጥቷል።

የቢሮ ኃላፊዋ ዶክተር ሀና የሺንጉስ  በዚህ ወቅት እንዳሉት የአገሪቱ የልማት ጉዞ የተሳካ እንዲሆን ተተኪ ትውልድ ለሆኑ ህጻናት አስፈላጊውን እንክብካቤና ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይጠይቃል፡፡

አገሪቱ ፈጣን የሆነ እድገት ለማምጣት በምትንቀሳቀስበት የለውጥ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ገልጸው በዚህ ወሳኝ ወቅት የነገ አገር ተረካቢ ህጻናት ላይ መስራት አገርን መገንባት መሆኑን አስገንዝበዋል።

የህጻናት እድገትና የአዕምሮ ብሰለት የሚጎለብተው ከ3 ዓመት እድሜያቸው በፊት በሚሰሩ ስራዎች በመሆኑ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ይህን በመገንዘብ ቢሮው ህጻናትን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በዛሬው ዕለት በሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሚገኝ የህጻናት ማቆያ እና በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አንድ የቀዳማይ ልጅነት እድገት ማእከል አስፈላጊውን ጥገና እና ግብአት በማሟላት ተመርቀዋል፡፡

እንደዚህ አይነት ማዕከላት በመዲናዋ መከፈት መጀመራቸው ልጆች ከእኩዮቻቸው ጋር እየተጣወቱ እንዲያድጉና ወላጆችም ሳይረበሹ ስራቸውን የሚሰሩበትን እድል እንደሚፈጥር ገልፀዋል፡፡

ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የከተማው ነዋሪዎችና ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ሊያደረጉ ይገባል ብለዋል።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ ዶክተር  ታምራት ዘላለም በበኩላቸው በዛሬው እለት በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አያት 4 ኮንደሚኒየም ሳይት  የቀዳማይ ልጅነት እድገት ማዕከል ተመርቆ ለነዋሪው መተላለፉን ገልጸዋል፡፡

ለማዕከሉ አስፈላጊውን እድሳት እና ግብአት ለመሟላት  4 ወራት እንደፈጀ ገልፀው ለዚህም ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ወጪውም በቢሮው እና በሌሎች አጋር አካላት ትብብር  መሸፈኑን ዶክተር  ታምራት ተናግረዋል።

ማዕከሉ 50 ህጻናትን በአንድ ጊዜ ማቆየት የሚችል ሲሆን 500 የሚሆኑ ህጻናትን ማጫወት የሚያስችል ስፍራ ያለው መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አያት 4 ኮንደሚኒየም ሳይት  ነዋሪ የሆኑት አቶ ሀብተልዑል ሀይሉ በበኩላቸው  በአካባቢው ልጆች  የሚጫወቱባቸው ምቹ ቦታዎች ባለመኖራቸው ተቸግረው እንደነበር አስታውሰዋል።

የዚህ ማዕከል መመረቅም ችግሩን እንደሚፈታው ጠቁመዋል።

የጋራ መኖሪያው ነዋሪዎች ማዕከሉን በአግባቡ በመጠበቅ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡

በሰኔ ወር በአፍሪካ ለ32ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ  ለ31ኛ ጊዜ የአፍሪካ ህጻናት ቀን ሲከበር ቆይቷል።

የዝግጅቱ የማጠቃለያ መርሀ ግብር የፊታችን ሰኔ 30 በወዳጅነት ፓርክ  እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

በእለቱም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉ ሲሆን ህጻናት የተለያዩ ጥቃቶች እንዳይደርሱባቸው ከላላ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እንደሚሰሩ በመግለጫው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም