ልማታችንን በማጠናከር ሀገራችን ወደሚገባት ከፍታ እንወስዳታለን-የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳ

198

ዲላ ሰኔ 28/2014 (ኢዜአ) "ውድቀታችንን የሚመኙ ጠላቶቻችንን እየተከላከልን ልማታችንን እያጠናከርን ሀገራችን ወደ ሚገባት ከፍታ እንወስዳታለን" ስሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው ተናገሩ።

በክልሉ በቡናና ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት እንዲሁም ህገወጥ ዝውውርን በመቆጣጣር የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ መዋቅሮች የማበረታቻ ሽልማትና እውቅና የመስጠት መረሃ ግብር ዛሬ በዲላ ከተማ ተካሂዷል።

ሽልማቱን የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳ በክልሉ በውስን አርሶ አደሮች ማሳ የተመዘገበው የቡና ምርታማነትን ለማስፋት ርብርብ ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በክልሉ ለሰብል ምርታማነት ያለውን ምቹ ስነ ምህዳርና አምራች ሰው ሃይል በማቀናጀት የምግብ ዋስትና በአጭር ጊዜ ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ህዝብን እርስ በእርስ ለማጋጨት የሚጥሩ ጸረ ሰላም የሆኑ አካላትን በመከላከልና የልማት ስራዎችን በማጠናከር ሀገራችን ወደ ከፍታ ልንወስዳት ይገባል ብለዋል።

በተለይ የተሻሻሉና በሽታ መቋቋም የሚችሉ የቡና ችግኞችን ከመትከል ጎን ለጎን የምርት ጥራትና ህገ ውጥነትን በመከላከል የአርሶ አደሩን ሕይወት ከመቀየር ባለፍ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ የምናደርገው ጥረት ማጠናከር እንደሚገባ አቶ ርስቱ አስገንዝበዋል።

በተያዘው አመት በክልሉ ከ32 ሺህ ቶን በላይ ቡናና ከ124 ሺህ ቶን በላይ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ እንደተቻለ የጠቀሱት ደግሞ የደቡብ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ዋና ዳይሬክተር አቶ ሬድዋን ከድር ናቸው።

ህገ ውጥ የቡናና ቅመማ ቅመም ዝውውርን ለመቆጣጠር በተደረገ ጥረትም ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቡና ምርት በቁጥጥር ስር መዋሉን ጠቅሰዋል።

በተጠናቀቀው በጀት አመት የዘርፉን ምርታማነትን ለማሳደግ ከ80 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ መተከሉን ተናግረዋል።

እንደ ክልል 32 ሺህ ኩንታል የቡናና ከ1 መቶ 24 ሺህ ቶን በላይ የቅመማ ቅመም ምርት ለማእከላዊ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል።

ዛሬ የተሰጠው ሽልማትና እውቅና ስነስርአት በቡና እደሳትና የግብይት ስርዓት፣ በህገ ወጥ ቁጥጥር፣ በቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች መሆኑን አብራርተዋል።

በመድረኩ የክልልና ከሁም ዞንና ወረዳዎች የተወጣጡ የስራ ሃላፊዎች የምርምር ተቋማት ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም