የመከላከያ ሪፎርም ሰራዊቱ ከፓርቲ ታዛዥነት ወጥቶ ህዝባዊና አገራዊ ሰራዊት እንዲሆን አድርጓል

318

ሰኔ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ)  የመከላከያ ሪፎርም ሰራዊቱ ከፓርቲ ታዛዥነት ወጥቶ ህዝባዊና አገራዊ አደረጃጀትና አስተሳሰብ እንዲኖረው ማድረጉን የ8ኛ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አሰፋ ቸኮል ገለጹ፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ በቆየበት የስልጣን ዘመን የኢትዮጵያን አንድነትና የሀገር ሉዓላዊነት ያስቀጥላሉ ያላቸውን ተቋማት በማፍረስ ተጠምዶ ነበር፡፡

ለአብነት የአገር መከላከያ ሰራዊቱን የአንድ አካባቢ ሰዎች በበላይነት እንዲይዙት በማድረግ አንድ አይነት አገራዊ አስተሳሰብ ያለው ሰራዊት ከመገንባት ይልቅ ህወሓት እንደ ፓርቲ የሚፈልገውን ጉዳይ ማስፈፀሚያ መሳሪያ አድርጎት ቆይቷል፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱን አንድነት በመናድ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቀድሞ የሸረበውን ሴራ እውን ለማድረግም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሰራዊቱ ላይ ጥቃት በመክፈት የሀገር ክህደት ፈጽሟል፡፡

በመከላከያ ሰራዊት የ8ኛ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አሰፋ ቸኮል ለኢዜአ እንዳሉት፤ የህወሓት የሽብር ቡድን አገር የማፍረስ ዕኩይ አላማውን ዕውን ለማድረግ ቀድሞ ሲሰራ የነበረው ሰራዊቱን መከፋፈል ነበር፡፡

በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ አባላት ላይ ጥቃት በማድረስ የአገር ክህደት የፈጸመውም "ሰራዊቱ የተከፋፈለ ነው፤ አንድነት የለውም" በሚል የተሳሳተ ግምገማ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የጦርነት ነጋሪት መጎሰምና አገር ማተራመስ የአዕምሯቸው ዕለታዊ ቀለብ ያደረጉት የሽብር ቡድኑ አባላት ለጥቃቱ ያነሳሳቸውም "ጦርነት ከእኛ በላይ የሚችል የለም" ከሚል ዕብሪተኝነትና በሰራዊት ግንባታ የመጣውን ለውጥ በሚገባ ካለመረዳት ነው ብለዋል፡፡

የመከላከያ ሰራዊት የአገራዊ ሰራዊት ቅርጽ የያዘው ከለውጡ በኋላ በተሰራ የሪፎርም ስራ ነው የሚሉት ሌተናል ጀነራል አሰፋ ቸኮል፤ ሰራዊቱ ከብሔር፣ ከሀይማኖትና ከፖለቲካ አጥር ወጥቶ አንድ አይነት አስተሳሰብ መያዙን ገልጸዋል፡፡

የመከላከያ ሰራዊት በፓርቲ ሰዎች እየተዘወረ የግል ንብረታቸው እስኪመስል ድረስ ሲቀለድበት እንደነበር አስታውሰው፤ የመከላከያ ሪፎርም ኢትዮጵያን የሚመሰል አገራዊ ሰራዊት እንዲኖረን አስችሏል ብለዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ ሪፎርሙ ኢትዮጵያዊ መሰረት ያላቸው ተቋማት በሴራ ከፍና ዝቅ ቢሉም ተመልሰው ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠራቸው የማይቀር መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የመከላከያ ሰራዊት ከለውጡ በኋላ ከአንድ ፓርቲ ታዛዥነው ወጥቶ ህዝባዊነትን የተላበሰ የሰራዊት አደረጃጀትና አስተሳሰብ የያዘበት ጊዜ አሁን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ከርቀት ሆነው የመከላከያ ሰራዊቱን ስም በሀሰት የሚያጠፉት ቀርቦ ካለማየትና እውነታውን ካለመረዳት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመከላከያ ሰራዊት ህወሓት በዘር ከፋፍሎ ባስቀመጠበት ቁመና ቢሆን ኖሮ ለሩብ ክፍለ ዘመን በዘለቀው ሴራው የተዘጋጀበት ጦርነት ራሱን ወደ መቀመቅ አይከተውም፤ ማሸነፍም ፈጽሞ አይታሰብም ነበር ብለዋል፡፡

በመከላከያ ተቋም የሰራዊት ግንባታ፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀረፃ እውን የሆነው ትልቅ የሪፎርም ስራ በመሰራቱ መሆኑን የገለጹት ሌተናል ጄኔራል አሰፋ፤ በዚህም ሰራዊቱ እራሱን እያደራጀና እያጠናከረ አስተማማኝ ቁመና ላይ መድረሱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም