ኢትዮጵያና ሱዳን በመካከላቸው ያሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት ተስማሙ

98

ሰኔ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ውዝግብን ጨምሮ በመካከላቸው ያሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት ተስማሙ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሱዳን የሽግግር መንግስት ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌተናል ጀነራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ጋር ዛሬ በኬንያ ናይሮቢ ተወያይተዋል።

መሪዎቹ በሁለትዮሽና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል።

ሁለቱ መሪዎች ስምምነት ላይ በተደረሰባቸው ጉዳዮች ዙሪያም በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያና ሱዳን ከሚያጋጯቸው ጉዳዮች ይልቅ የሚያቀራርቧቸውና በጋራ የሚሰሩባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ ብለዋል።

በመሆኑም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያሉ የልዩነት ጉዳዮችን በሰለጠነ መንገድ በውይይት በመፍታት የሁለቱን ሀገራትና ህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ተስማመተናል ነው ያሉት።

ሁለቱን ሀገራት ወደ ግጭት ከሚያስገቡ ድርጊቶች መታቀብ እንደሚያስፈልግም መግባባት ላይ መደረሱንም እንዲሁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም በሀገራቱ መካከል ያሉ አንዳንድ ችግሮችን ኮሚቴ በማቋቋምና ዓለም አቀፍ መርሆን ባከበረ መልኩ በውይይትና በድርድር ለመፍታት መስማማታቸውን ነው የጠቀሱት።

ኢትዮጵያና ሱዳን በሰላምና በልማት ጉዳይ በትብብርና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለመስራትና ግንኙነታቸውን ለማጠናከርም መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ሁለቱ መሪዎች በሀገራቱ መካከል ውዝግብ በፈጠሩ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት መወያየታቸውን አንስተው፤ ውይይታቸውም ፍሬያማ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተናገሩት።

ኢትዮጵያ ከሱዳን ወንድም ህዝብ ጋር በትብብር ለመልማትና በሰላም ለመኖር ፅኑ አቋም እንዳላትም አረጋግጠዋል።

የሱዳን የሽግግር መንግስት ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌተናል ጀኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን በበኩላቸው፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር እንደ ወንድም በመወያየት በሀገራቱ መካከል ያሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተስማምተናል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያና ሱዳን ጠንካራ መሰረት ያለውና የቆየ ወዳጅነት ያላቸው እህትማማች ሀገራት ናቸው ያሉት አልቡርሃን፤ ከግጭት ምንም አናተርፍም ብለዋል።

በመሆኑም በቀጣይ ለሁለቱ ህዝቦች ተጠቃሚነትና የወደፊት አብሮነት በጋራ እንሰራለን ሲሉም ተደምጠዋል።

በህዳሴ ግድብና በድንበር ጉዳይ ያሉ አለመግባባቶችን ያለግጭት በሰላማዊ መንፈስ ለመፍታትና ቁርጠኝነታችንን በተግባር ለማሳየትም ከስምምነት ላይ ደርሰናል ብለዋል። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም