የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አዲስ ድረ-ገጽ ይፋ አደረገ

649

አዲስ አበባ ሰኔ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በመዲናዋ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን የሚያስተዋውቅና መረጃ የሚሰጥ ድረ-ገጽ ይፋ አደረገ።

ቢሮው ድረ-ገጹን ያስመረቀው ከአዲስ አበባ ቴክኒክ ሙያ ሥልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር ነው

ድረ-ገጹ በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ሲሆን፤ በቀጣይ በሌሎች የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ነው የተገለጸው።

ድረ-ገጹ በከተማዋ ካሉት የቱሪስት መዳረሻዎች፣ ሙዚየሞች፣ ሐውልቶች፣ ፓርኮች ቴአትር ቤቶች በተጨማሪ አጠቃላይ ተግባራቱንም የሚያስተዋውቅበትና መረጃ የሚሰጥበት እንደሆነም ተጠቁሟል።

የቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሣው፤ የድረ-ገጹ ሥራ ላይ መዋል የተለያዩ መረጃዎችን በአንድ ጊዜ ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል

የመረጃዎቹም ተደራሽነት በመዲናዋ ብቻ እንዳይወሰንና በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲዳረስ ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ድረገፁ እንደፌስቡክ ፣ ቲውተር ፣ ቴሌግራም ፣ ኢንስታግራም ካሉት ማኅበራዊ ድረገፆች ጋር የተሳሳረ እንደሆነም ተናግረዋል።

ድረ-ገጹ ከኅብረተሰቡ የሚመጡ አስተያየቶችን መቀበልና ሥራ ላይ ማዋልን ጨምሮ አገልግሎት ፈላጊዎች ማሟላት በሚገባቸው ጉዳዩች ላይ ግልጽ የሆነ መረጃ የሚቀመጥበት እንደሆነም አንስተዋል።

የቢሮው የመረጃ ግንኙነት አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ እሸቱ፤ ድረ-ገጹ ከዚህ በፊት ያልተካተተውን የኪነ-ጥበብ ዘርፍ አቅፎ መያዙን ጠቁመዋል።

ከወቅቱ ቴክኖሎጂ ጋር የሚሄድ በመሆኑም ነባር መረጃዎችን ለማሻሻልና አዳዲስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማድረስ ይረዳል ነው ያሉት።

ድረ-ገጹን ያበለፀጉት የአዲስ አበባ ቴክኒክ ሙያ ሥልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ባለሙያዎች አብረሃም ረታ እና አብዱልከሪም ሰዒድ እንደገለፁት፤ ድረ-ገጹ በየጊዜው መሻሻል እንዲችል ሆኖ የተዘጋጀ ነው።

በመሆኑም በቀጣይ የመዲናዋ የትራንስፖርት፣ የቪዛ አገልግሎት፣ የአየር ንብረት ሁኔታና ሌሎችም መረጃዎችን በማካተት ድረ-ገጹን አመቺ በሆነ መልኩ ለማበልጸግ መታሰቡን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም