የክልሉን የማዕድን ሃብት በአግባቡ ለምቶ ጥቅም ላይ እንዲውል በትኩረት እየተሰራ ነው -አቶ አሻድሊ ሃሰን

73

አሶሳ ፤ ሰኔ 28 / 2014 (ኢዜአ) :- የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማዕድን ሃብትን በአግባቡ ለምቶ ለሃገር ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ላይ እንዲውል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን አስታወቁ።

በአሶሳ ከተማ ለክልሉ ወርቅ አምራቾች  የምስጋና ፕሮግራም  እየተካሄደ ነው።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት፤  ከክልሉ ተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ ለሃገር ኢኮኖሚ እንዲውል ታቅዶ እየተሰራ ነው።

በተለይም ባለሃብቶችን በስፋት ወደ ወርቅ፣ እምነበረድ፣ ከሰል ድንጋይ እና ሌሎችም ማዕድን ልማት እንዲገቡ ማድረግ ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።

እየጨመረ የመጣውን አነስተኛ የወርቅ  አምራች ማህበራት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማደራጀት ሌላው ጥረት እንደሆነ አመልክተዋል።  

ማዕድን በአግባቡ ካልተያዘ  ለግጭት እንደሚዳርግ ያመለከቱት አቶ አሻድሊ፤በሂደትም  የአካባቢውን ደህንነት ማስጠበቅ  እንደሚገባ ተናግረዋል።

በተለይ በአሶሳ ዞን በሚገኙ ባህላዊ የወቅር አምራቾች ለማምረት ኬሚካል እንደሚጠቀሙ ጠቅሰው ፤በሳይንሳዊ መንገድ ካልተደገፈ በሰው ፣ እንስሳትና ተፈጥሮ ሀብት ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በህገወጥ መንገድ ድንበር አቋርጦ የሚወጣ ወርቅ መኖሩን ጠቁመው፤ ችግሩን ለማቃለል  የተጀመሩ የማስተካከያ እርምጃዎች እንደሚጠናከሩ አስታውቀዋል።

የክልሉ ማዕድን ልማት አጀንሲ ዋና ዳይሬክተር  አቶ ናስር መሃመድ፤ በክልሉ ባለፉት 10 ወራት 2ሺህ 200 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሄራዊ ባንክ መግባቱን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ለ183 አምራቾች ፈቃድ መሰጠቱን ጠቅሰው፤ ከአምስት ዓመት በፊት 86 ብቻ እንደነበሩ አስታውሰዋል።  

ባህላዊ ወርቅ አምራቾች ማህበራት ቁጥር ደግሞ ባለፉት ሶስት ዓመታት  26 የነበሩት በበጀት ዓመቱ ወደ 234 አድገዋል ብለዋል።  

ይህም የሃገራዊ ለውጡ ውጤት ነው ያሉት አቶ ናስር፤  ውጤቱ እንዲቀጥል ህብረተሰቡ ሠላሙን እንዲጠብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም