ለምክክር መድረኩ ስኬታማነትና ለሰላም መረጋገጥ የበኩላችንን እንወጣለን ---የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አመራሮች

69

ደብረ ብርሃን ሰኔ 28/2014(ኢዜአ) ወጣቱን በማስተባበር ለሀገራዊ የምክክር መድረኩ ስኬታማነትና ለሰላም መረጋገጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶ ሊግ አመራሮች ገለጹ ።

የሊጉ አባላት ''በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ'' በሚል መሪ ሀሳብ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎችን በደብረ ብርሃን ከተማ ትላንት አስጀምረዋል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወጣት ሜሮን አበበ ለኢዜአ እንደገለጸችው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሀገራዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት መጠናከር የጎላ ሚና አለው።

በተያዘው ክረምት በዞኑ ከ40 ሺህ በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተለያዩ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ተግባራትን እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ለሚካሂደው የምክክር መድረክ ስኬታማነት ከበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጎን ለጎን ወጣቱ ስለ ሰላም መጠበቅና በምክክሩ ጠቀሜታ ላይ ህብረተሰቡን እንዲያነቁ ይሰራል ብለዋል።

ከደቡብ ክልል ከየም ልዩ ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወጣት ሐብታሙ መኩሪያ በበኩሉ የተለያየ ጽንፈኛ ቡድኖች በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ልማትን ለማፋጠን የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፉ እኩይ ተግባን ሲፈጽሙ ይስተዋላሉ ብሏል።

"ባለፈው አገዛዝ የተዘራብን የዘረኝነት አረም ጊዜ ጠብቆ ዛሬ ላይ ውስጣዊ ችግር እየፈጠረ ይገኛል" ያለው ወጣቱ ኢትዮጵያን ለማተራመስና ለማፍረስ የሚሰሩ የውጭ ጠላቶች አጋጣሚውን ለመጠቀም እየሰሩ ይገኛል ሲል ተናግሯል።

በኢትዮጵያዊያን በፖለቲካ ውስጥ የሃሳብ ልዩነት በየትኛውም የዓለም ሀገራት ያለ መሆኑን በመገንዘብ በልዩነቶቹ ላይ የሃሳብ ትግል በማድረግ ለዘላቂ ለሰላም ፣ አንድነትና እድገት በጋራ መትጋት አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።

ወጣቱ በተለይ በአሁኑ ወቅት የህዝብን በሰላም ወጥቶ የመግባት እንቅስቃሴ ሳጋት ላይ የሚጥሉና ሰላምን የሚያውኩ ጽንፈኛ ቡድኖችን መመከት ላይ ወጣቱ የድርሻውን መወጣት አለበት ነው ያለው።

የአገራዊ የምክከር መድረክ ስኬታማ መሆኑን በሀገሪቱ የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮችን በመቅረፍ ለዘላቂ ሰላምና እድገት መረጋገጥ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን በመገንዘብ ወጣቱ ጠቃሚና ሚዛናዊ ሀሳቦችን በማበርከት የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፏል።

ሀገራዊ የውይይት መድረኩ የታለመለትን ግብ እንዲያሳካ የበኩሉን እንደሚወጣም ወጣት ሐብታሙ ተናግሯል።

''አባቶቻችን የውጭ ጠላትን አሳፍሮ በመመለስ ነፃነቷ የተከበረ ሀገር አስረክበውናል፤ እኛም የእነሱን ታሪክ ልንደግም ይገባል'' ያለው ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ ወጣት ደረጀ አበራ ነው።

"ወጣቱ ባደረገው ትግል የመጣውን አገራዊ ለውጥ ለማደናቀፍ ንጹሃንን በመግደልና ከመኖሪያቸው በማፈናቀል እየደረሰ ያለውን ጥፋት በተደራጀ አግባብ ሊመክት ይገባል"  ነው ያለው።

ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት በውይይት እንጂ በግጭት አለመሆኑን በመረዳት ወጣቱ  በመንደር አጀንዳ ሰጪ አካላት ሳይከፋፈል ሀገርን ወደተሻለና ጠቃሚ ጉዞ እንድትጓዝ መሰረት ለሚጥለው የምክክር መድረኩ ስኬት የድርሻችን እንዲወጣ ሰራለሁ ብሏል።

በክረምት የበጎ ፈቀድ አገልግሎት ማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ላይ የፌደራልና የክልል፣ የወጣቶች ሊግ አመራሮችና አባላትን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም