ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል

60
አዲስ አበባ መስከረም 2/2011 የደቡብ ሱዳን ሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስገነዘቡ። 33ኛው የኢጋድ የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል። ከውይይቱ አጀንዳዎች መካከል የደቡብ ሱዳን ሁለት ተፋላሚ ወገኖች የሰላም ስምምነት የመጨረሻው ፊርማ አንዱ ነው። ሁለቱ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ላለፉት ሶስት ወራት በሱዳን ካርቱም ወደ ሰላም ለመምጣት ድርድር ሲያደርጉ ቆይተዋል።ይህን ተከትሎም በተካሄደው የኢጋድ ስብሰባ ላይ ዛሬ ምሽት የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል። በዚሁ ጊዜ የኢጋድ የወቅቱ ሊቀ መንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዳሉት "ስምምነት መፈራረም ብቻ በቂ አይደለም፤ ለተግባራዊነቱም መስራት ይገባል"። ለዚህም ኢጋድ በቁርጠኛነት እንደሚደግፍም አረጋግጠዋል። የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት ለቀጠናው ምሳሌ እንደሚሆን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፈቃደኝነት ካለ የትኛውም አለመግባባት በውይይት እንደሚፈታ አክለዋል። በተጨማሪም የኢትዮ-ኤርትራ ስምምነት አፍሪካ ችግሮቿን በራሷ መንገድ መፍታት እንደሚትችል ማሳያ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውስተዋል። በቀጠናው የሚታዩ መሰል ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም በአገራቱ መካከል የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠርና ቀጠናውን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ እንደሚገባም አክለው ገልጸዋል። በመጨረሻም በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል ሲፈጠር የቆየው የእርስ በርስ ጦርነት እልባት ማግኘቱ "ለደቡብ ሱዳን ንጹሃን ዜጎች አሳዛኙ ምዕራፍ የሚዘጋበት እንደሚሆንም ተስፋ አደርጋለሁኝ" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። የኢጋድ ዋና ጸሐፊ አምባሳደር ኢንጂነር  መህቡብ ማሊም በበኩላቸው ሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች ወደ ስምምነት ለመምጣታቸው አስተዋጽኦ ላበረከቱ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገራት ምስጋና አቅርበዋል። ሱዳን ፣ ኡጋንዳና ኬንያን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ተጠባቂ ለሆነው የሰላም ስምምነት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የሚመሰገኑ መሆናቸውንም አክለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም