መንግስት በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ለሚሰማሩ ኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ይሰራል-ዶክተር አርከበ ዕቁባይ

2547

አዲስ አበባ መስከረም 2/2011 መንግስት በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ለሚሰማሩ ኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ ስልቶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የጠቅላይ ሚንስትሩ ልዩ አማካሪ ዶክተር አርከበ ዕቁባይ ተናገሩ።

ዶክተር አርከበ ይህን ያሉት ኢትዮጵያ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ለሚሰማሩ ኢንቨስተሮች ያላትን ምቹ ሁኔታ ከቻይና ብሄራዊ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምክር ቤት ለመጡ ልዑካን ባብራሩበት ወቅት ነው።

ልዑኩ የምክር ቤቱን አመራሮችና  በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ መሰማራት የሚፈልጉ የቻይና ባለሃብቶችን ያቀፈ ነው።

የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሰን ሩዝሂ እንዳሉት፤ ቻይና በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ አሃዱ ብላ ከጀመረች ገና 40 ዓመታት ቢሆናትም ዘርፉ አሁን ላይ በአገሪቱ አመታዊ ምርት ላይ ቀላል የማይባል ድርሻን ይዟል።

አሁን ላይ የቻይና የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ በዓለም ዋነኛ ተወዳዳሪ መሆኑን አውስተው፤ ለዚህ መሰረታዊ ምክንያቱ ደግሞ ጠንካራ የአቅርቦት ትስስር መፍጠር መቻላችን ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያም ከዚህ ተሞክሮ መውሰድ እንዳለባትም በማውሳት።

የኢትዮጵያ መንግስት በተለይ ወጪ ንግድ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑ እንደሚያስመሰግነውም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ሰፊ የሰው ጉልበት መያዟ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንደሚያደርጋት ገልጸው፤ የሰው ሃይሏን በበቂ ሁኔታ ለማሰልጠን ትኩረት እንድትሰጥም ጠቁመዋል።

“የአፍሪካው ንጹሁ መንግስት” ሲሉም ኢትዮጵያ በኢንዱስተሪ ፓርኮቿ ላይ ለአረንጓዴ ልማት የሰጠችውን ትኩረት አሞካሽተዋል።

ዶክተር አርከበ እቁባይ በበኩላቸው መንግስት ዘርፉን ማሳደግ የሚችሉ ሶስት መሰረታዊ የፖሊሲ ውሳኔዎችን አስቀምጦ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ጨርቃ ጨርቅና አልባሳትን ጨመሮ የሌሎች ዘርፎችን ቀጣይነት ለማስጠበቅ ሲባልም የኢንድስትሪ ፓርኮችን ከአረንጓዴ ልማት ጋር የተሳሳሩ እንዲሆኑ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለዘርፉ እድገትና ምርታማነት ወሳኝ ከሆነው የሰው ሃይል አቅርቦት በተጨማሪ በኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ሁሉ ከሌሎች አገራት በተሻለ መልኩ ሃይልን  በተመጣጣኝ ዋጋ እንደምታቀርብም አውስተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህን ጉዳዮች አጠናክሮ ለመቀጠል አቅጣጫ ማስቀመጡን ገልጸው፤ ልዑኩም ይህን በመረዳት በአፋጣኝ ኢንቨስት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስት በኢንዱስትሪ ፓርኮች የተጀመረውን የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለማስፋት እንዲሁም በቀጠናው የሚገኙ ወደቦችን በጋራ አልምቶ ለመጠቀም ያለው ቁርጠኝነት ለኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ጨምረው ገልጸዋል።