የአፍሪካ ሱፐር ሊግ የእግር ኳስ ውድድር ሊጀመር ነው

466

ሰኔ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ)የአፍሪካ ሱፐር ሊግ የእግር ኳስ ውድድር እ.አ.አ በ2023 እንደሚጀመር የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) አስታወቀ።

የካፍ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትናንት ባደረገው ስብሰባ የሱፐር ሊግ ውድድሩ እንዲካሄድ ወስኗል።

የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ ከ40 ክለቦች ጋር በተደረገ ውይይት የመጀመሪያው ውድድር እ.አ.አ ነሐሴ 2023 እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

አጠቃላይ ለውድድሩ የ100 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ይዘጋጃል።

ገንዘቡም ከስፖንሰሮችና ከማስታወቂያ እድሎች ይሰበሰባል ብለዋል።

የአፍሪካ ሱፐር ሊግ ውድድር አላማ በአህጉሩ ለሚገኙ የእግር ኳስ ክለቦች የውድድር አማራጭ ማስፋትና የሚያገኙትን ገቢ ማሳደግ እንደሆነ ተገልጿል።

በሱፐር ሊጉ መጫወት የሚፈልግ ክለብ የእግር ኳስ አካዳሚና የሴቶች ክለብ ሊኖረው እንደሚገባ ተነግሯል።

ካፍ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ክለቦች እንዴት ይመረጣሉ? ወይም የውድድሩን አቀራረብ የተመለከተ መረጃ ይፋ አላደረገም።

የካፍ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትናንት ባደረገው ስብሰባ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግና የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታዎች ወደ ነበረበት የደርሶ መልስ የውድድር ይዘት እንዲመለስ ወስኗል።

በተያያዘ ዜና እ.አ.አ ሰኔ 2023 በኮትዲቭዋር አስተናጋጅነት ሊካሄድ የነበረው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ መራዘሙን ካፍ አስታውቋል።

በኮትዲቯር በሚኖረው የአየር ንብረት ሁኔታ ዝናባማ በመሆኑ ምክንያት “ኃላፊነት ወስደን በወቅቱ ውድድሩን ማካሄድ ስላልፈልግን ” ነው ብለዋል የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ።

የአፍሪካ ዋንጫው እ.አ.አ በጥር እና የካቲት ወራት እንደሚካሄድና በቀጣይ የውድድሩ ማጣሪያ ጨዋታ ቀናት በቀጣይ ይፋ እንደሚደረጉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም