የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አንዳንድ አካባቢዎች ከባድ ዝናብና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችል አሳሰበ

179

ሰኔ 26/2014/ኢዜአ/ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ እርጥበት አዘል አየር በአጭር ጊዜ ተጠናክሮ በሚቀጥሉት ቀናት ከባድ ዝናብ በመፍጠር ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

በኢንስቲትዩቱ የአየር ሁኔታና የአየር ጸባይ ትንበያ ዳይሬክተር ወይዘሮ ጫሊ ደበሌ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ወደ አገራችን የሚገባው እርጥበት አዘል አየር ካለፉት ሳምንታት በበለጠ በቀጣዮቹ ሳምንታት ሊጠናከር እንደሚችል ትንበያዎች ያሳያሉ።

በዚህም የጎርፍ አደጋ ሥጋት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ አደጋ እንዳይፈጠር ከወዲሁ የመከላከል ሥራ ማከናወን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተለይ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ ወንዞችና ተዳፋታማ አካባቢዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተጠናከረ የጥንቃቄ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በአንዳንድ ቦታዎች ላይ እርጥበት አዘል አየር በአጭር ጊዜ ተጠናክሮ ከባድ ዝናብ በመፍጠር ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁመው፤ በተለይ በከፍተኛ ቦታዎችና፣ በደጋ አካባቢ የሚዘንበው ዝናብ በዝቅተኛ አካባቢዎች ላይ የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በመካከለኛ እና ሰሜን ምስራቅ የአገሪቱ ክፍሎች እና በዝቅተኛ ቦታዎችም ላይም በአጭር ጊዜ የሚጥለው ዝናብ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ቦዮችን በመጥረግና በመክፈት፣ የውሃ መውረጃ በማዘጋጀት ጎርፍ ወደ ቤትና የእርሻ ማሳ እንዳይገባ ቅድመ ዝግጅት ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አልፎ አልፎ የሚያጋጥመው የመብረቅ አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ህብረተሰቡ የራሱን ጥንቃቄ መውሰድ አለበት ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዚህም በአብዛኛው የክረምት ተጠቃሚ ከሆኑት የደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች በስተቀር ሌሎች አካባቢዎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ ዝናብ ሊያገኙ ይችላሉ ሲሉ ጠቁመዋል።

ከሰኔ ወር በተሻለ መልኩ በሀምሌ ወር የተጠናከረ የዝናብ መጠንና ስርጭት ሊኖር ይችላል ብለዋል።

በሰሜን፣ ምስራቅ እና መካከለኛ የሀገሪቱ አካባቢ ላይ መደበኛ የዝናብ ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ትንበያዎች እንደሚያሳዩ ተናግረው፤ ዝናቡ ለግብርና፣ ለውሃ ሃብትና ለሌሎችም ስራዎች በጎ ጠቃሜታ ስላለው ህብረተሰቡ በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባል ብለዋል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት የዝናቡ ሁኔታ ወደ ሰሜን፣ ሰሜን ምስራቅና ምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍሎች እየተስፋፋ መምጣቱን ተናግረዋል።

በዚህም በ24 ሰዓት ውስጥ ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ ከባድ ዝናብ በአንዳንድ የምስራቅ አማራ፣ ምዕራብ አማራ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች መመዝገቡን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም