አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን አጠናቆ ወደ ዝግጅት ምዕራፍ መግባቱን አስታወቀ

142

ሰኔ 26/2014/ኢዜአ/ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ስራዎችን አጠናቆ ወደ ዝግጅት ምዕራፍ መግባቱን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።


መንግስት በኢትዮጵያ ያሉ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት እና አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በማሰብ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሙ ይታወሳል።

ኮሚሽኑ በህዝበ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ተቋቁሞ የኮሚሽኑ ሰብሳቢና አመራሮች ከተሾሙለት በኋላም በይፋ ወደ ቅድመ ዝግጅት ስራ መግባቱ ይታወቃል።

በዚህም ኮሚሽኑ ከመንግስት ኃላፊዎች፣ ከክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ትውውቅ አድርጓል።

በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ኮሚሽኑን የማደራጀት ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን የድርጊት መርሃ-ግብር በማውጣትም ወደ ዝግጅት ምዕራፍ የሚያስገቡ ስራዎችን አከናውኗል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ከሚሽኑ በአሁኑ ወቅት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን አጠናቆ ወደ ዝግጅት ምዕራፍ መግባቱን ተናግረዋል።

በዝግጅት ምዕራፉም ለስራ የሚያስፈልገውን በጀትና ስትራቴጂክ እቅድ ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ ሲሆን በአጭር ጊዜ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጸድቆ ወደ ስራ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

በዚሁ ምዕራፍ በአገራዊ ምክክሩ ሂደት የሚዘጋጁ የውይይት መድረኮችን የሚመሩና የሚያወያዩ ግለሰቦችንና ባለድርሻ አካላትን የመምረጥ፣ ስልጠና የመስጠት ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቅሰዋል።

በዚህም መሰረት ስለአገራዊ ምክክሩ ከአወያዮችና ተወያዮች ጋር በሚሰሩ ተግባራት ዙሪያ መግባባት ላይ በመድረስ ወደ ምክክር የሚገባበትን ምቹ መደላድል እንደሚፈጠር ነው የተናገሩት።

ፕሮፌሰር መስፍን አክለውም፤ የዝግጅት ምዕራፉ በሚቀጥለው ዓመት የመጀመሪያ ወራት ሊጠናቀቅ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ዝግጀቱ እንደተጠናቀቀም በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ ውይይትና ምክክር እንደሚኖር ጠቁመው፤ ኢትዮጵያውያን በውይይት ችግሮቻቸውን በማስወገድ ለቀጣዩ ትውልድ መልካም ውርስን ማስተላለፍ አለባቸው ብለዋል።

በአገሪቱ የዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት እንዲረጋገጥና ሰላም እንዲሰፍን የጥይት ጩኸትን በማቆም ሁሉም ወደ ውይይት መግባት አለበት ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም