ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት በተግባር እንዲያሳዩ ጥሪ ቀረበ

97

አርባምንጭ፤ ሰኔ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) ተመራቂ ተማሪዎች የሀገር ሠላምና ልማት ግንባታን በመደገፍ በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት በተግባር እንዲያሳዩ ጥሪ ቀረበ።

የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች  በመጀመርያ፣ ሁለተኛና ሶሰተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ከ2ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ደርዛ ባደረጉት ንግግር፤   ተመራቂዎች  በቆይታቸው የተቋሙን ሰላም በማስከበር  ትምህርታቸውን በአግባቡ ማጠናቀቅ ችለዋል።

ይህም ተማሪዎች ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳዩበትና ለአቀዱት ዓላማ ቆራጥነትን በተግባር ያረጋገጡበት ነው ብለዋል።

የሀገሪቱ ሠላምና ልማት ግንባታ በመደገፍ  በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት በተግባር እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢትዮጵያ ሜትሮዎሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ተመራቂዎች  የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ስራዎችን በማከናወን የተጣለባቸውን ሃላፊነት መወጣት አለባቸው ብለዋል።

በተለይ ሀገሪቱ ለያዘችው ዘላቂ የእድገት ጉዞ  መሳካት አስተዋጽኦ በማበርከት ሃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባ  ተናግረዋል።

በውሃ ምህንድስና በከፍተኛ ማዕረግ  የተመረቀው  ደሳለኝ አበራ በሰጠው አስተያየት፤ ሀገሪቱ የጀመረችውን የሰላምና የእድገት ጉዞ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል።

ሀገርና ህዝብ የጣለበትን ሃላፊነት ለመወጣት ቀን ከሌሊት ጠንክሮ እንደሚሰራ የተናገረው ደግሞ በሶፍትዌር ምህንድስና በማዕረግ የተመረቀው  መሐመድ አህመድ ነው።

አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ካሰመረቃቸው መካከል ዘጠኝ በዶክትሬት እና 490  በሁለተኛ ዲግሪ   ሲሆን፤ ከአጠቃላዮቹም  662 ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል።

ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅትም የሚያስተምራቸው ከ29ሺህ በላይ ተማረዎች እንዳሉትም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም