የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ብልጽግና ለማረጋገጥ ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት ውጤት ተገኝቷል-አቶ አወሉ አብዲ

139

ነቀምቴ፤ ሰኔ 25 /2014(ኢዜአ) ፡- የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ባለፉት ሶስት ዓመታት ችግሮችን በመቋቋም ብልጽግና ለማረጋገጥ ለግብርናው ልማት በሰጠው ትኩረት በተከናወነው ስራ ውጤት መገኘቱን የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ ገለጹ።

በምሥራቅ ወለጋ ዞን  ከ756 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ግንባታቸው የተጠናቀቁ  የልማት ፕሮጀክቶች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኘበት ተመርቀዋል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት  ምክትል ፕሬዚዳንት እንዳሉት፤ መንግሥት ባለፉት ሶስት  ዓመታት ያጋጠሙትን የተፈጥሮና ሰው ሰራሸ ችግሮችን በመቋቋም  ብልጽግና ለማረጋገጥ ለግብርናው እድገት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ውጤት አስገኝቷል።

የበጋ የስንዴ መስኖ ልማትን በማስፋፋት በሚሊዮን የሚቆጠር  ኩንታል  በማምረት የአርሶ አደሩ ገቢ እንዲጨምር ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤ ምሥራቅ ወለጋም ትልቅ ሀብት ያለው አከባቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

ክልሉ የአከባቢውን ልማት ካረጋገጠ ለሌላው የሀገሪቱ  ክፍል ጭምር የሚተርፍ  በመሆኑ የክልሉ መንግሥት ለአካባቢው  ልማት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

የመንገድ የመሠረተ ልማትን በማስፋፋት ቡና፣ ማርና  አቡካዶን ጨምሮ  ለሌሎች የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ትኩረት በመስጠት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ከዚህም ሌላ የክልሉ መንግሥት ከሁለት ዓመት በፊት 11 ሺህ፣ ባለፈው ዓመት ደግሞ 16ሺህ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ማስመረቁን  አቶ አወሉ አስታውሰዋል።

ዘንድሮ ደግሞ  ከ20ሺህ የሚበልጡ ፕሮጀክቶችን በማስመረቅ የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የምሥራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወጋሪ ነገራ እንደተናገሩት፤  በዞኑ በ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወጪ 347 የልማት ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ ቆይተዋል።

ከነዚህም  በ79 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ተግንብቶ ትናንት የተመረቀው   ባለ ሰባት  ወለል የጊቤ ዲዴሣ የገበሬዎች የሕብረት ሥራ ዩኒዬን ህንጻ እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።

የባህል ማዕከል፣የስብሰባ አዳራሽ፣ የጤና ጣቢያ ማስፋፊያ፣ትምህርት ቤቶች በዞኑ ግንባታቸው ተጠናቆ ለምረቃ የበቁት  ሌሎቹ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን አቶ ወጋሪ አስረድተዋል።

የዞን ሕዝብ ለሰላም መከበርና ልማት መረጋገጥ የሚያርገውን ትብብር አጠናክሮ የተመረቁትንም ፕሮጀክቶች በመንከባከብ በተገቢው እንዲጠቀሙበት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የተሳተፉበት የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር በነቀምቴ ከተማ ሲካሄድ፤ በከተማዋ አስተዳደር በ110 ሚሊዮን ብር ወጪ  ለሚገነባው የወጣቶች ማዕከል   የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም