ኦህዴድ የድርጅቱን ቀጣይ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ ይወስናል ተብሎ የሚጠበቅ ጉባዔ ቀጣይ ሳምንት ያካሄዳል

77
አዲስ አበባ መስከረም 2/ 2011 የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ በቀጣዩ ሳምንት የድርጅቱን ቀጣይ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ ጨምሮ በርካታ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎች ይተላለፉበታል ተብሎ የሚጠበቅ ጉባዔ ያካሄዳል። ዘንድሮ ለዘጠነኛ ጊዜ የሚካሄደው ጉባዔው “የላቀ ሀሳብ ለበለጠ ድል” በሚል መሪ ሃሳብ ከመስከረም 8 እስከ 10 ቀን 2011 ዓ.ም በጅማ ከተማ እንደሚካሄድም ታውቋል። በኦህዴድ ጽህፈት ቤት የገጠር አደረጃጀት ሃላፊ አቶ አድሱ አረጋ እንዳሉት በጉባኤው በርካታ አዳዲስ ወጣት ምሁራን በማዕከላዊ ኮሚቴ አመራርነት ይመረጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ያለፉት ሶስት ዓመታት የድርጅት እና የፖለቲካ ስራዎች የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት፣ የኦዲት እና ቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርት ቀርቦም ይመከርበታል። የፓርቲው ቀጣይ ስትራቴጂክ አቅጣጫዎችም ቀርበው ውይይት ተደርጎባችው እንደሚፀድቁ ይጠበቃል። ከዚህም በተጨማሪ ፓርቲው በአዲስ ስያሜ፣ አርማ እና መዝሙር ራሱን 'ሪብራንድ' ያደርጋል ብለዋል። የጉባዔው የመክፈቻ ስነ ስርዓት ከ6 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት በደማቅ ስነ ስርአት የሚከፈት ሲሆን 1070 ተሳታፊዎች በድምፅ 275 ሰዎች ደግሞ በታዛቢነት ይሳተፋሉ ይላል ከአቶ አዲሱ አረጋ ያገኘነው መረጃ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም