ዘመነ ክረምት

1207

በኢትዮጵያ የወቅቶች አከፋፈል መሠረት የክረምት ወቅት ከዘመነ መከር፣ በጋና በልግ ቀጥሎ የሚመጣ አራተኛ ወቅት ነው።

ክረምት ከረመ፣ ከርመ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን የውሃ፣ የነጎድጓድ፣ የመብረቅና የዝናብ ወቅት የሚል ፍቺ እንዳለው የአማርኛ መዝገበ ቃላትና ድርሳናት ያስረዳሉ።

የክረምት ወቅት ተብሎ በዋናነት የሚነገረው ጊዜ ከሰኔ 25 እሰከ መስከረም 26 ያለው ወቅት ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ከሚገባበት ቀን ቀድሞ ሊገባና ከሚወጣበት ቀንም ዘግይቶ ሊያበቃ ይችላል።

የክረምት ወቅት የዘርና የአረም እንዲሁም የውሃ ወቅት በመሆኑ ገበሬው እርሻውን የሚያካሂድበት ወሳኝ ጊዜ ነው።

ምድርም አረንጓዴ ለብሳ በአትክልት፣ አዝዕርትና አበቦች ተሸፍና መታየት ትጀምራለች፣ ይህም የውበትና የመልካም ተስፋ ተምሳሌት አለው።

ክረምት ምንም እንኳን የቅዝቃዜና የጭጋግ ሁኔታን ቢይዝም የሰው ልጅ መኖርያ የሆነችው ምድርን በማረስረስ ምግብ እንድታበቅልና ንጹህ አየር እንድትሰጥ የሚደርጋት እጅግ አስፈላጊ የተፈጥሮ ዑደት ነው።

ክረምት በየትኛውም ክፍለ አኅጉር ወቅቶችን እየቀያየረ ምድርን ሲያድስ የሰው ልጆችንም ሕልውና አብሮ በማደስ ሰውና ክረምት ያለውን ቁርኝት ዘላለማዊ አድርጎታል።

በክረምት የሚመጣው ትሩፋት በመከርና በበጋ የሚታይ ውጤት እንደመሆኑ እኛም ዛሬን እንደ ክረምት በመቁጠር ለበጋ የሚበቃ ጠንካራ ስራ መስራት አለብን።

ኢትዮጵያ ከምንም ጊዜ በላይ ሰፊ የክረምት ስራ እንዳለባት አውቀን ሰላሟን ለመጠበቅ፣ ድህነትን ለማሸነፍና ሉዓላዊነቷን ለማስከበር እጅ ለእጀ ተያይዘን መስራት ይኖርብናል።

የክረምት ዝናብ እንደ ጉልበት፣ የክረምት ፀሐይ እንደ ተስፋ፣ የምድርን አረንጓዴ መልበስ በጠንካራ ተግባር እንደሚመጣ ልምላሜ ቆጥረን ለመከርና በልግ የምንጠብቀውን መልካም ውጤት ዛሬ እንስራ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም