ነባር ብሔራዊ ፓርኮች ችግር ውስጥ በመሆናቸው ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተገለጸ

92
አዲስ አበባ  መስከረም 2/2011 በኢትዮጵያ ነባር ብሔራዊ ፓርኮች ትልቅ ችግር ውስጥ በመሆናቸው ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማት ጥበቃ ባለስልጣን አመለከተ። ባለስልጣኑ የፓርኮችን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ በአገሪቱ የሚገኙ ፓርኮች ለችግር መጋለጣቸውን አመልክቷል። የባለስልጣኑ ዋና ዳሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ እንደተናገሩት፤ በተጠናቀቀው 2010 ዓ.ም የነበሩ አለመረጋጋቶችን ተከትሎ በፓርኮች ላይ ጉዳት ደርሷል። በአመቱ አዲስ የተከፈቱ 3 ፓርኮችን ጨምሮ በአገሪቱ የሚገኙ 27 ፓርኮች ለተለያየ ችግር መጋለጣቸውን ያመለከቱት አቶ ኩመራ ነባር ፓርኮች የከፋ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። በፓርኮች አካባቢ የሚኖረው ማህበረሰብ የተጠቃሚነት ጥያቄ በማንሳት ፓርኮችን ማቃጠል፣ መመንጠር እንዲሁም የተለያዩ ማእድናትን እናወጣለን በሚል በመቆፈር ፓርኮቹ ላይ ጉዳት አድርሰዋል። አቢያታ ሻላ ብሔራዊ ፓርክ ማእድንና አሸዋ ለማውጣት፣ ባሌ ተራሮች ወረራ፣ ነጭ ሳር ምንጣሮ፣ ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ሰደድ እሳትና መሬት ወረራ መፈጸሙን ለአብነት ጠቅሰዋል። እነዚህ ፓርኮች ያሉበት ደረጃ በጣም የከፋና አሳሳቢ መሆኑን በመግለጽ የዞን አመራሮች በትኩረት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። ችግሮችን ህግ በማስከበር ለመፍታት የተሰሩ ስራዎች ቢኖሩም በብሔራዊ ፓርኮች ላይ የተጋረጡ አደጋዎችን ለማስቆም ከአቅም በላይ እንደነበር አስረድተዋል። የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማት ጥበቃ ባለስልጣን ችግሮችን ለመፍታት ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የተጠቃሚነት ጥያቄዎች ለመመለስ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በዚህም ከ42 ሺህ በላይ ጊዜያዊ የስራ እድል በመፍጠር ከፓርክ ጥበቃ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አግኝተዋል። ሆኖም ችግሩ የከፋ በመሆኑ የዞንና የፌደራል ተቋማትን ጥረት የሚፈልግ በመሆኑ በጋራ ሊሰራ ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል። በ2010 ዓ.ም ፓርኮችን ከጎበኙ ከ133 ሺህ በላይ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጎብኝዎች ከ120 ሚሊዮን በላይ ብር ገቢ መገኘቱን በመግለጫው ተነግሯል። ህገ ወጥ የእንስሳትና እንስሳት ውጤቶች ንግድ ለመከላከል ከሚመለከታቸው ጋር በቅንጅት በመሰራቱ 20 ኪሎ ግራም የዝሆን ጥርስን ጨምሮ ሌሎች ወደ ውጭ ሊወጡ ሲሉ ተይዘዋል። ባለ ስልጣኑ ህገ ወጥነትን ለመከላከል በቦሌ አለም አቀፍ አየር መንገድና ሌሎች መውጫ በር አካባቢ አነፍናፊ ውሾችን በተያዘው አመት ስራ ላይ እንደሚያሰማራ ጠቁሟል። በኢትዮጵያ በ1960 ከተቋቋሙት ሰሜንና ሰንቅሌ ብሔራዊ ፓርኮች ውጪ ሌሎች አሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኙና ትኩረት የሚሹ መሆናቸውም ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም