በአቅራቢያቸው የጤናና የትምህርት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የሰሜን ሸዋ ነዋሪዎች ገለጹ

80
ፍቼ ግንቦት 10/2010 የጤናና የትምህርት መሰረተ ልማት በአቅራቢያቸው ተመቻችቶላቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ 27ኛው የግንቦት 20 በዓልን ምክንያት በማድረግ ኢዜአ ካነጋገራቸው የዞኑ ነዋሪዎች መካከል በፍቼ ከተማ የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ደመና አበራ እንዳሉት ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ትምህርት ቤት በአቅራቢያቸው አልነበረም፤ ልጆቻቸውም ሳይማሩ ቀርተዋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ትምህርት ቤቶች እየተስፋፉ በአቅራቢያቸው ተደራሽ መሆናቸው አራት ልጆቻቸውን  በአጭር ርቀት ውስጥ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው  ተምረው ራሳቸውን እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡ የግራር ጃርሶ ወረዳ አርሶ አደር ወይዘሮ ሸዋዬ ታምሩ በበኩላቸው በአካባቢያቸው መንግስት ባመቻቸላቸው የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የጤና አገልግሎት በአካባቢያቸው ተደራሽ ከመሆኑ በፊት ነፍሰ ጡር እናቶች በልምድ አዋላጅ ይጠቀሙና  በዚህም ጉዳት ይደርስባቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አሁን ግን ይህ ችግር እንደሌለና እሳቸውም ሶስት  ልጆቻቸውን በሆስፒታል ለመውለድ እንደቻሉና የህክምና እርዳታ በማግኘት እስካሁንም  በመጠቀም ላይ እንዳሉ ተናግረዋል። የቤት ለቤት የምክርና የጤና አግልግሎት እያገኙ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ በዚህም በተለይ ከገቢያቸው ጋር የተጣጣመ  ቤተሰብ እንዲኖራቸውና የኑሮ ዘዴያቸው እንዲቀየር እንደረዳቸውም ጠቁመዋል። በፍቼ  ቀበሌ ሶስት ነዋሪ  መምህር  ሜሮን ማሞ  እንደገለጹት መንግስት ለችግሮች መወገድ በሰጠው ትኩረት ለዘመናት በከተማው የነበረው የጤናና የትምህርት ተቋማት ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል። በተለይ የእናቶችና ህፃናት ሞትን ለመቀነስ በጤና ተቋማት የሚሰጡው ክትባት ጤናቸውን ለመጠበቅ ያስቻለ መሆኑን ከራሳቸውን ተሞክሮ ማየታቸውን ተናግረዋል። የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ደለሳ  ወልዴ በበኩላቸው ከ1983 ዓ.ም በፊት በሰሜን ሸዋ  ሆስፒታል እንዳልነበረ አስታውሰው አሁን ግን አምስት ሆስፒታሎች ተገንብተው ህብረተሰቡ በአቅራቢያው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ሁለት ብቻ የነበሩት ጤና ጣቢያዎች ወደ 63 ማደጋቸውንና በዞኑ ባሉ 268 ቀበሌዎች ደግሞ  በእያንዳንዳቸው የጤና ኬላዎች  ተገንብተው የህክምናና የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 15 እና የተማሪዎቹ ቁጥር ደግሞ 31 ሺህ የነበሩት በአሁኑ ወቅት ከ700 በላይ የመጀመሪያ ደረጃና ከ285 ሺህ የሚበልጡ ታዳጊ ወጣቶች የመማር እድል ማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት  ኃላፊ   አቶ ሁሴን  አልዩ  ናቸው ። ሁለት ብቻ የነበረውን  የዞኑ የሁለተኛ ደረጃ  ትምህርት ቤት ብዛትም በአሁኑ ወቅት መሰናዶን ጨምሮ  ወደ 50 ማደጉንም አመልክተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም