ኢትዮጵያን በሁለንተናዊ ብልፅግና የአፍሪካ ተምሳሌት የማድረጉ ጥረት የሁሉንም ዜጋ ርብርብ ይጠይቃል-ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ

117

አርባ ምንጭ ሰኔ 23/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን በሁለንተናዊ ብልፅግና የአፍሪካ ተምሳሌት የማድረጉ ጥረት የሁሉንም ዜጋ ርብርብ እንደሚጠይቅ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ፡፡

 ህዝቡ ከመንግስትና ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የአከባቢውን ሰላምና አንድነትን ማስጠበቅ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ተምሳሌት የማድረግ ጉዞ ሁለንተናዊና ዕድገትን ማስመዝገብ ያለመ ነው ብለዋል።

በለውጥ ሂደቱ ውስጥ የፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ድፕሎማሲያዊ ብልጽግና ምዕራፎች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡

''በሀገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲና ፌዴራሊዝም እንዲረጋገጥ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳዮች የሚሳተፉበትና ተጠቃሚ የሚሆኑበት  ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ'' ብለዋል።

 አካታች ሀገራዊ ምክክሩና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ጥረት  በዋቢነት እንደሚጠቅስ ተናግረዋል።

ከኢኮኖሚያዊ ብልጽግና አንፃር በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድንና አይሲቲ ልማት ወቅቱን የዋጀ ውጤት ለማስመዝገብ መንግስት አበክሮ እየሰራ መሆኑን ዶክተር ቢቂላ አስረድተዋል፡፡

በቀጣይ ሁለት ዓመታት ወደ ውጭ የግብርና ምርቶችን ለመላክ እቅድ መያዙን አመልክተው፤ ''የቱሪዝምና ማዕድን ሀብቶችን በማልማት የኢኮኖሚ ስብራታችን ለመደገፍ እየተሰራ ይገኛል'' ብለዋል፡፡

''ኢትዮጵያ የበርካታ ማህበራዊ ሀብቶች ባለፀጋ እንደመሆኗ መጠን የህዝቡን አንድነት፣ አብሮነትና የባህል ትስስርን በማጠናከር ብሎም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር በመስራት፣ የጋራ ልማትና ተጠቃሚነት በማጉላት በማህበራዊና ድፕሎማሲያዊ ብልፅግና የአፍሪካ ተምሳሌት ሀገር እናደርጋለን'' ብለዋል።

 የሀገሪቱ ለውጥ ያልተመቻቸው የውስጥና ውጭ ጠላቶች ሀብቶቿን ለመቀራመት እንዲሁም  ሰላምና ጠንካራ መንግስት እንዳይኖር ዜጎችም አንገታቸውን ደፍተው እንዲኖሩ የግጭት ቀጠና ለማድረግ እያሴሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

''ኢትዮጵያን ማፍረስ አይቻልም'' ያሉት ዶክተር ቢቂላ፤ የዜጎችን ሰላም የሚነሱ አካላትን ሥርዓት በማስያዝ የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያን በአፍሪካ በሁለንተናዊ ብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ እንዲሳካ ህዝቡ የአከባቢውን ሰላም በማስጠበቅ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን በበኩላቸው መንግስት ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲና እውነተኛ ፌዴራሊዝም ለማረጋገጥ  እየሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች በሀገር ግንባታና በህዝቡ አንድነትና አብሮነት ላይ ትኩረት በማድረግ ህብረተሰቡን ለልማት ማነሳሳት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

 በህግ ማስከበሩ ስራ ህዝቡ በንቃት መሳተፍ  እንደሚገባው ተናግረዋል።

ህወሃትና ሸኔ ዕድሜያቸውን ለማራዘም ለዘመናት ተከባብረው የኖሩ የኢትዮጵያ ህዝብ እያጋጩ አንዱ ለሌላው ስጋት እንዲሆን እያደረጉ  ነው ያሉት ደግሞ በአሜሪካ ኒውዮርክ የሚኖሩት ወይዘሮ ወሰንየለሽ እሸቱ ናቸው፡፡

 ''በመተባበርና በመተሳሰብ አንድነታችንን ጠብቀንሀገርን ማስቀጠል ይገባናል'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም