መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ውጤቶች ለተጠቃሚው ለማድረስ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገለጸ

208

ጎባ ፤ ሰኔ 23/2014 ( ኢዜአ ) መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ወደ ተጠቃሚው ዘንድ እንዲደርሱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገለጸ። 

ለሁለት  ቀናት ሲካሄድ የቆየው የዩኒቨርሲቲው ዘጠነኛው ዙር ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ ዛሬ የተጠናቀቀ ሲሆን፤   በተለያዩ የትኩረት መስኮች ላይ ያተኮሩ 77  የጥናትና ምርምር ውጤቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሰን ሽፋ በወቅቱ እንዳሉት፤ ተቋሙ  የማህበረሰቡን ችግርና ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ምርምሮችን በማካሄድ ላይ ይገኛል።

በተለይ በግብርና፣ ቱሪዝም፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ  የትኩረት መስኮች ላይ የልህቀት ማዕከል ለመሆን አቅዶ እየሰራ  ነው ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው ምሁራን የቀረቡ  77 የምርምር ጥናቶችን በመምረጥ ወደ ማህበረሰብ ፕሮጀክት በመቀየር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል ነው ያሉት ዶክተር ሀሰን።

ተቋሙ  ከዚህ በፊት በተናጠል ይሰሩ የነበሩ ጥናትና  ምርምር ተግባራት በማቀናጀት ወደ ሜጋ ፕሮጀክት ከፍ እንዲሉ መደረጉን አመልክተዋል።

በዚህም በዩኒቨርሲቲው የሚካሄዱ ምርምሮች ችግር ፈቺ እንዲሆኑና ለምርምር ስራ የሚመደበው በጀት እንዳይባክን እገዛ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በዩኒቨርሲቲ  የተካሄዱ የጥናትና ምርምር ውጤቶች  ለተጠቃሚው ለማድረስ  ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። 

ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል መምህርና ተመራማሪው  አቶ ከማል አብደላ በሰጡት አስተያየት፤ በዩኒቨርሲቲው ምሁራን በተለያዩ የትኩረት መስኮች ላይ የሚካሄዱ ችግር  ፈቺ  ጥናቶችና የምርምር ውጤቶች ወደ  ህብረተሰቡ ወርደው ተግባር ላይ በመዋል ረገድ ክፍተቶች ይስተወላሉ ብለዋል።

የምርምርና ጥናት ውጤቶች ወደ ታች ወርደው ህብረተሰቡን  ተጠቃሚ ያላደረጉት ተመራማሪዎች በየደረጃው ከሚገኙ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርበው ባለመስራታቸው እንደሆነ ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት ተቀራርበው በችግሮቻቸው ላይ የሚመካከሩበት መድረክ መፍጠሩ ችግሩን ለመፍታት ጉልህ ድርሻ እንዳለው ነው የገለጹት።

ዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላትን የሚያገናኝ መድረክ ችግሮችን በማቃለል  የተሻለ ለመስረትያግዛል ያሉት ደግሞ ከምዕራብ አርሲ ዞን በኮንፈረንሱ  የተሳተፉት አቶ ከድር ኡስማን ናቸው።

የምርምር ውጤቶቹ ወደ ታች ወርደው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት አብረው ለመስራት ከስምምነት መደረሳቸውም ተመልክቷል።

በኮንፈረንሱ  የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ፣ ከባሌና ምስራቅ ባሌ እንዲሁም  ምዕራብ አርሲ ዞን  የመንግሥት ተቋማት የተወጣጡና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም