ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ በኦሮሚያ ክልል ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገለጹ

243

ነገሌ፣ ሰኔ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ፡፡

በጉጂ ዞን ነገሌ ከተማ በክልሉ መንግሥት በ289 ሚሊዮን ብር የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።

በምረቃው ወቅት ፕሬዝዳንቱ እንደገለጹት፤ በሀገራዊ ለውጡ ማግሥት የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ለማደናቀፍ ሌት ተቀን እየሰሩ ቢሆንም አልተሳካላቸውም።

አሸባሪው ህወሃት የክልሉን ህዝብ ለ27 ዓመታት ሲዘርፍና ሲገድል አንድ ጥይት ያልተኮሰው አሸባሪው የሸኔ ቡድን በህዝብ ትግል የመጣውን ለውጥ ለማደናቀፍ መሯሯጡ ዓላማ ቢስነቱን እንደሚያረጋግጥ ተናግረዋል።

ሸኔ የወያኔ ፈረስ በመሆን የኦሮሞን አባቶችን ገድሏል፣ እናቶችና ህጻናትን ደፍሯል፣ ንብረት ዘርፏል፤ አቃጥሏል፣ አውድሟል ብለዋል።

የለውጡ መንግሥት ለኦሮሞ ህዝብ የገባውን ቃል በማክበር የጀመራቸውን በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች አጠናቆ እያስመረቀ እንደሆነም አመልክተዋል።

በነገሌ ከተማ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት፣ የዞኑ ገቢዎች፣ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ጽህፈት ቤት ህንጻ ግንባታዎችን በአብነት አንስተዋል።

ህዝብ በሽብር ቡድኖች የሀሰት አሉባልታ ሳይደናገር የአካባቢውን ሰላምና ልማቱን እንዲጠብቅ ጠይቀዋል።

የጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ኡዶ በዞኑ በዚህ ዓመት 175 የመንገድ፣ የውሀ፣ የጤናና የትምህርት መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል።

ከነዚህ መካከል አገልግሎት መስጠት የጀመረው የገናሌ ነገሌ የንጹህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክት አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።

ፕሮጀክቱ የአካባቢውን አርብቶ አደሮች ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በከተማው በ179 ሚሊዮን ብር የተገነባው አዳሪ ትምህርት ቤት በሁለት የሀገር ውስጥና በአራት ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ትምህርት እንደሚሰጥም አስታውቀዋል፡፡

አዳሪ ትምህርት ቤቱ 18 መማሪያ ክፍሎች፣ የተማሪዎች ማደሪያ፣ ቤተ መጻህፍት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የመሰብሰቢያና የመመገቢያ አዳራሾችን ያካተተ እንደሆነ ገልጸዋል።

የአዶላ ከተማ ነዋሪና እጩ አባገዳ ሳሙኤል ቦሩ ግንባታቸው ተጠናቆ እየተመረቁ ያሉት መሰረተ ልማቶችና ተቋማት በሀገራዊ ለውጡ የተመለሱ የዞኑ ህዝብ የዓመታት የመልማት ጥያቄዎች እንደሆኑም ገልጸዋል።

በፕሮጀክቶቹ እኩልና ለፍትሀዊ ተጠቃሚ ለመሆን ሁላችንም በጎሳና በብሄር ሳንከፋፈል የክልሉን መንግስት በማገዝ ልንተባበር ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም