ኢትዮጵያ የገጠሟትን ወቅታዊ ችግሮች እድትሻገር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የላቀ ሚናቸውን ተወጥተዋል

176

ሰኔ 23/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የገጠሟትን ወቅታዊ ችግሮች እድትሻገር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የላቀ ሚናቸውን መወጣታቸውን የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ገለጸ።

ሁለተኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ''የነቃ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ለሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት'' በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በይፋ ተከፍቷል።

በመረሃ ግብሩ ላይ የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዴዎን ጢሞትዮስ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰና ለሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዳይሬክተር ሄኖክ መለሰ፤ በመረሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት  ኢትዮጵያ የገጠሟትን ወቅታዊ ችግሮች እድትሻገር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የላቀ ሚና የነበራቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከግሉ ዘርፍና ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የዜጎችን አሁናዊና ዘላቂ ፍላጎት በማሟላት ለልማትና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም በሀገሪቷ የሰላም፣የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት መጠናከር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚናቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤  በለውጡ ሂደት በርካታ ችግሮችን በመሻገር በተለይ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ብዙ መሰራቱን ገልጸዋል።

በቀጣይም በተለይ በሴቶች፣ በህጻናት፣ በወጣቶችና አረጋዊያን ዙሪያ ከሁሉም አካላት ጋር መንግስት በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።                                         

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት አመታት ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች ብዙ ፈትና ማለፏን አንስተዋል።

በተለይ የሰላም እጦቱ በጤናው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ችግር ማስከተሉን ጠቅስው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የደረሱ ውድመቶችና ጉዳቶችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ በነበረው ጥረት የማይተካ ሚና መወጣታቸውን ገልጸዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጂማ ዲልቦ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ ባለድርሻ አካላት በቅንጅትና በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት በኢግዚቢሽንና ባዛር፣ በፓናል ውይይቶችና ልዩ ልዩ ኩነቶች ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሰኔ 25 ቀን 2014 ዓ.ም የሚቆይ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም