ጉባኤው ሴቶች የሠላም አምባሳደርነት ሚናቸውን እንዲወጡ አቅጣጫ አስቀምጠ

158

ሐዋሳ፤ ሰኔ 23/2014 (ኢዜአ)፡ ሴቶች ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት የአምባሳደርነት ሚናቸውን እንዲወጡ አቅጣጫ መቀመጡን የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ አስታወቀ ፡፡

ሊጉ አቅጣጫውን ያስቀመጠው በሐዋሳ እየተካሄደ ባለው የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ አንደኛ ጉባኤ ላይ ነው፡፡

በጉባኤ አጀንዳዎችና በጉባኤው በተነሱ አንኳር ጉዳዮች  ሊጉ ዛሬ በሐዋሳ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የፓርቲው የሴቶች ሊግ ምክትል ፕሬዚዳንትና የሊጉ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ መስከረም አበበ እንደገለጹት በሊጉ የመጀመሪያ ጉባኤ በቀረቡ ሰነዶች፣ በሊጉ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ እንዲሁም የኢንስፔክሽንና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን ሪፖርት ላይ ውይይት መካሄዱን ተናግረዋል።

 ጉባኤው የሀገር ሠላምና የዜጎች ደህንነት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መወያየቱን የተናገሩት ወይዘሮ መስከረም፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ንፁን ዜጎች  በአሸባሪዎችና ጽንፈኞች የጥቃት ሰለባ እየሆኑ እንደሚገኙ መመልክቱን ጠቅሰዋል ፡፡

ጉባኤው በክፍተቶች ላይ በመምከርም ሴቶች የአብሮነት እሴቶችን በማጠናከር በሀገራዊ ሠላም ላይ  የአምባሳደርነት ሚናቸውን እንዲወጡ የሊጉ አመራርና አባላት በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታውቀዋል ፡፡

ሴቶች ልጆቻቸውን ህብረብሔራዊነት የተላበሰ ኢትዮጵያዊ አመለካከት ባለቤት አድርገው እንዲገነቡ ትውልድን የመቅረፅ ማህበራዊ ሃላፊነታቸው  መወጣት እንዳለባቸው በጉባኤው አጽንኦት መሰጠቱን ተናግረዋል።

ችግሮች ከመፈጠራቸው አስቀድሞ የመከላከል ሥራ ላይም የሴቶች ንቁ ተሳትፎ ሊኖራቸው እንደሚገባም ተመላክቷል።

መንግስት እያከናወነ ያለው የሕግ ማስከበር ሥራ ስኬታማ እንዲሆንም መረጃዎችን ከመስጠት ጀምሮ ሴቶች ከመንግስት ጎን ቆመው እገዛ እንዲያደርጉ ጉባኤው መምከሩን ጠቁመዋል ፡፡

ሊጉ  ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ አባላት እንዳሉት ጠቁመው፤ በመስኖ ሥራ፣ በከተማ ግብርናና በሌሎች የግብርና ልማት ሥራዎች ላይ ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ሴቶች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ፈጥኖ በመቀበልና ተግባር ላይ በማዋል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ ሊጉ በትኩረት መስራት እንዳለበትም አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል ፡፡

በሥራ ዕድል ፈጠራ በተለይ በዕድሜ ገደብ ምክንያት የተዘዋዋሪ ፈንድ ብድር ማግኘት የማይችሉ አዋቂ ሴቶች የብድር አቅርቦት እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመስራት መመከሩንና አቅጣጫ መቀመጡን አስታውቀዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር፣ በተግባር ተኮር ትምህርት ፣ በጤና መድኅን ተጠቃሚነትና በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይም የሴቶች ተሳትፎ እንዲጎለብት ሊጉ በትኩረት መስራት እንዳለበት በጉባኤው መጠቆሙን ገልጸዋል ፡፡

“የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና ” በሚል መሪ ሀሳብ በሐዋሳ  በመካሄድ ላይ ያለው ጉባኤ  ነገም ቀጥሎ እንደሚውል ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም