በሲዳማ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰፋፊ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስታወቁ

81

ሀዋሳ ፤23/2014 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል የህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰፋፊ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ፡፡

ክልሉ እንደ ክልል የተደራጀበትን ሁለተኛ ዓመት የምስረታ በዓል  ሰኔ 27/2014ዓ.ም እንደሚያከብርም ተገልጿል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ  አቶ በየነ ባራሳ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ በሃገሪቱ የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ የሲዳማ ህዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄው ምላሽ አግኝቷል፡፡

ጥያቄው ምላሽ ማግኘቱን ተከትሎም ባለፉት ሁለት ዓመታት ህዝቡን ወደ ልማት በማስገባት ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡

እንደ ክልል ሲደራጅ ከህዝቡ ጋር በተደረገ ውይይት ይነሱ የነበሩ የልማት ጥያቄዎች ተለይተው  ደረጃ በደረጃ ለመመለስ  ሰፊ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ በቀዳሚነት ሲነሳ የነበረውን የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ ከ600 ሚሊየን በሚበልጥ ወጪ ከ1ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን መገንባቱን ጠቅሰዋል።

የመንገድ ግንባታዎቹ ቀበሌን ከቀበሌ፣ከወረዳና ከክልል የሚያገናኙ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋኑን ለማሳደግ በተከናወነው  ስራም 37 በመቶ የነበረው የክልሉ የውሃ ሽፋን 49 በመቶ ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የሃይል አቅርቦትን ለማመቻቸት በተደረገው ጥረትም ሰፋፊ የኤሌክትሪክ አስተላላፊ መስመሮች መዘርጋታቸውን የተናገሩት  ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በጤናው ዘርፍ አዳዲስ የጤና ተቋማት ግንባታዎች፣ ነባርን የማጠናከርና በግብአት የማደራጀት ስራ መከናወኑን አንስተዋል፡፡

የክልሉ ህዝብ ሃገሪቱ  ፈተና ውስጥ በገባችበት እስከ ግንባር ከመዝመት ጀምሮ ለውጡን ለማደናቀፍ የመጣውን አጥፊ ለመመከት  ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

ሃገራዊ አንድነቱን ለማስቀጠል ክልሉ በመደገፍ ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች መሆናቸውን የገለጹት   ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ኢትዮጵያዊያን ተከባብረው የሚኖሩበት ክልል ለማድረግ የተሰራው ስራም ውጤታማ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ ያለው ሰላም ለቱሪዝም ተመራጭ እንዳደረገውና አዳዲስ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች እንዲመጡ ማስቻሉንም ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመመለስ  የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያጠናከር  አመልክተው፤ የተገኙ ድሎችን ማስቀጠል በሚያስችል መልኩ የክልሉ የምስረታ በዓል  በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት የተከናወኑ የልማት ስራዎች ጉብኝት፣ የፓናል ውይይትና፣ የትግሉን ሰማእታት የሚዘክሩ የተለያዩ ፕሮግራሞች እንደሚኖሩም አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም