ወጣቶች ሀገርን በማስከበር ያከናወኑትን አኩሪ ተግባር በልማት እየደገሙት ነው- ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

118

ድሬዳዋ ፤ ሰኔ 23/2014 (ኢዜአ) ወጣቶች የሀገር ሉአላዊነት ለማስከበር እያከናወኑ ያለው አኩሪ ተግባራት በዘላቂ ልማቱ ላይ ለመድገም እየተረባረቡ መሆናቸውን የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።

ሚኒስትሯ  ዛሬ በድሬዳዋ ተገኝተው ሀገር አቀፉ  የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት ፤ ወጣቶች ባለፉት ዓመታት ባከናወኗቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

በብዙ ቢሊዮን የሚገምት ገንዘብ ከውጪ በማዳንም በሀገሪቱ ምጣኔ ሃብታዊና  የማህበራዊ አገልግሎት ችግሮች ትርጉም ባለው መንገድ እንዲቀንሱ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ ፤በመላው ሀገሪቱ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ  እየተሳተፉ የሚገኙ ወጣቶች የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር ያከናወኑትን አኩሪ ተግባራት በልማቱ ላይ እየደገሙት ነው።

ዘንድሮም የጀመሩትን የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ለማጠናከር በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች የላቀ ስራ ለመከወን እንቅስቃሴዎች ጀምረዋል ብለዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው፤ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች የተከናወኑ የልማት ተግባራት በአስተዳደሩ የማህበራዊ አግልግሎት ጥያቄዎችን በመሠረታዊነት እየፈታ መሆኑን ገልጸዋል ።

ለተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

በመረሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ  የተሳተፉ ወጣቶች የጀመሩት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ከሚያስገኘው የልማት ጥቅሞች በዘለል የተለያዩ ወግና ባህልን በመለዋወጥ ህብረ ብሔራዊ አንድነታቸውን ለማጠናከር እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

የችግረኛ አረጋውያንን ቤቶች የማደስና በአዲስ የመስራትን እንዲሁም ችግኝ በመትከል መረሃ ግብሩ ዛሬ በድሬዳዋ በይፋ ተጀምሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ  ሚኒስትሯን ጨምሮ ሌሎችም የፌደራልና የአስተዳደሩ አመራሮች እንዲሁም ወሰን ተሻጋሪ ሀገር አቀፍ የበጎ ፈቃድ አገልገሎት ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም