ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር ጉዳይ ያላቸውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ መፍታት አለባቸው-ሙሳ ፋኪ ማህማት

72

ሰኔ 22 ቀን 2014(ኢዜአ)“የአፍሪካ ሕብረት አባል የሆኑት ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር ጉዳይ ያላቸውን አለመግባባት በሕብረቱ የድንበር ፕሮግራም ማዕቀፍ በሰላማዊ መንገድ መፍታት አለባቸው” ሲሉ የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ገለጹ።

የኢትዮጵያ መንግስት የድንበር ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት “በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው ወታደራዊ ውጥረት አሳስቦኛል” ብለዋል።

ሁለቱ ወንድማማች አገራት ከወታደራዊ እርምጃ በመቆጠብ ያሉባቸውን የትኛውንም ውዝግቦች በውይይት መፍታት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር በቅርቡ የተከሰተው የድንበር ግጭት አገራቱ ያሉባቸውን ውስጣዊ ችግሮች ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ለማበጀት ላሳዩት ፍላጎት እንቅፋት መሆን እንደሌለበት አመልክተዋል።

ከዚህ አኳያ የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት የሆኑት ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር ጉዳይ ያሉባቸውን “ውዝግቦች” በሕብረቱ የድንበር ፕሮግራም ማዕቀፍ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ሙሳ ፋኪ ጥሪ አቅርበዋል።

ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የወንድማማችነት ግንኙነት ያላቸው እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት(የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት) መስራች የሆኑት ኢትዮጵያና ሱዳን ለቀጠናው መረጋጋትና የጋራ ደህንነት ሲባል በአስቸኳይ ሁሉንም ግጭቶች እንዲያቆሙ አሳስበዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የድንበር ፕሮግራም እ.አ.አ በ2007 የተቋቋመ ሲሆን የሕብረቱ አባል አገራት መዋቅራዊ ግጭት የመከላከል አቅማቸውን የማጠናከር ስራ አካል እንደሆነ የሕብረቱ መረጃ ያሳያል።

በድንበር ማካለል፣በድንበር ተሻጋሪ ትብብርና አቅም ግንባታ አማካኝነት ሰላም፣ደህንነትና መረጋጋትን ማምጣት የፕሮግራሙ ዋና አላማ ነው።

በተያያዘ ዜና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) ዋና ጸሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የሰሞኑ የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ጉዳይ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

May be an image of text

ሁለቱ እህትማማች አገራት ውጥረትን ከሚያባብሱ ድርጊቶች በመቆጠብ በጉዳዩ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የዲፕሎማሲ አማራጭን ብቻ መከተል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም