በአቦካዶ ልማት ላይ በመሳተፋችን የተሻለ ተጠቃሚ እየሆንን ነው ---አርሶ አደሮች

247

ባህር ዳር፤ ሰኔ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰሜን ሜጫ ወረዳ አርሶ አደሮች የቆጋ መስኖን በመጠቀም ካለሙት የአቦካዶ ልማት የተሻለ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናገሩ።

አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ከለማው አቡካዶ 3 ሺህ 516 ኩንታል ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑም ታውቋል።

የሰሜን ሜጫ ወረዳ አርሶ አደር ደረበ አብተው ለኢዜአ እንደገለጹት ለውጭ ገበያ የሚቀርብ አቦካዶ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ማልማት ከጀመሩ አምስት ዓመት ሆኗቸዋል።

የአቦካዶ ልማቱን በግብርና ባለሙያ ክትትል ታግዘው በኩታ ገጠም እያለሙ መሆኑን ተቅሰው ባለፈው ዓመት ከተከሉት 214 የአቦካዶ ተክል ላይ የሰበሰቡት 93 ኩንታል ምርት ለውጭ ገበያ በመላኩ 200 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

የዘንድሮ የገበያ ዋጋ ካለፈው ዓመት የተሻለ በመሆኑ በመጪው ወር100 ኩንታል የአቦካዶ ምርት ለውጭ ገበያ ላኪዎች ለማስረከብ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ከምርቱ ሽያጭም 500 ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኙ ነው የገለጹት።

በቀጣይ  ምርቱን በራሳቸው አቅም ለውጭ ገበያ ለማቅረብ 150 አርሶ አደሮች በህብረት ስራ ማህበር መደራጀታቸውን ነው አርሶ አደሮቹ የጠቆሙት።

የቆጋ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ አቢዮት ብሩ በቆጋ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ 260 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በአቦካዶ መልማቱን ገልጸዋል።

በልማቱ ላይ 845 አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸው 5 ሺህ 13 ኩንታል የአቦካዶ ምርት እንደሚጠበቅ ነው የገለፀጹት።

ከሚገኘው ምርት ውስጥ 3 ሺህ 516 ኩንታሉ ከአርሶ አደሮች ጋር ውል በፈጸሙ 3 ባለሃብቶች በኩል ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ዋጋውም ባለፈው ዓመት በኪሎ ይሸጥ ከነበረበት 20 ብር ዘንድሮ ወደ 53 ብር በመጨመሩ አርሶ አደሮቹ የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

ወደ ዘርፉ ልማት ያልገቡ ሌሎች አርሶ አደሮችም የሚያስገኘውን ጥቅም በመመልከታቸው ወደልማቱ እንዲገቡ መነሳሳት ተፈጥሯል ነው ያሉት።

በዘንድሮው የክረምት 800 አርሶ አደሮችን ወደ ዘርፉ ልማት በማስገባት 40 ሺህ የአቦካዶ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁንም አስታውቀዋል።

ስራአስኪያጁ እንዳሉት ለችግኝ መትከያ የሚሆን 96 ሄክታር መሬት ተለይቶ የቅየሳና የጉድጓድ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ከተሰበሰበው የአቦካዶ ምርት 1 ሺህ 652 ኩንታል ምርት ወደ ተለያዩ ሀገራት መላኩን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም