የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች ዉስጥ እንደሚሰጥ ተገለፀ

150

ሰኔ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ)የፈተና ሰርቆትና ማጭበርበርን ለማስቀረት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች ዉስጥ እንደሚሰጥ የትምህርት ሚኒስቴር ገለፀ።

በደቡብ ክልል በሆሳዕና፣ በወራቤና በወልቂጤ ከተሞች የሚገኙ ሁለተኛ ደረጃና ሞዴል ትምህርት ቤቶችን የጎበኙት የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከተማሪዎችና ከትምህርት ቤቶቹ ማህበረሰብ ጋር ቆይታ ነበራቸው።

በወቅቱም የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በትምህርት ቤቶች ሳይሆን በዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

እንደሚኒስትሩ ገለጻ፤ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደግፎ መስጠት እስከሚጀመር በዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ ይቀጥላል።

የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርሲቲ እንዲሰጥ የተወሰነው የፈተና ሰርቆትና ማጭበርበርን ለማስቀረት ታስቦ በመሆኑ ተማሪዎች ትምህርት በስራና በታታሪነት የሚገኝ መሆኑን አውቀው በርትተው መማርና ማጥናት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርትን ጥራትን ለማሻሻል በአጠቃላይና ከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፎች ሌሎችንም የተለያዩ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ መሆኑንም ፕሮፌሰር ብርሀኑ ጠቁመዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ በጉብኝታቸው ወቅት ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራ ማኖራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም