የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ልምምድ የሰላምና አብሮነት ማጎልበቻ እንጂ የውጥረትና መገፋፋት ምክንያት ሊሆን አይገባም- ዶክተር ለገሰ ቱሉ

189

ሰኔ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የተጀመረው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ልምምድ የሰላምና አብሮነት ማጎልበቻ እንጂ የውጥረትና መገፋፋት ምክንያት ሊሆን እንደማይገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ።

የጥላቻ ንግግሮችንና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭቶችን በመታገል ጠንካራ አገር መገንባት ይገባልም ነው ያሉት።

የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን "የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃን እየታገልን የዴሞክራሲ ሥርዓትን እንገነባለን" በሚል መሪ ሐሳብ ምክክር በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ፤ በኢትዮጵያ አዲስ የዴሞክራሲ ሥርዓት ልምምድ እየተደረገ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

በዚህ ሂደት ግን የጽንፈኝነትና አክራሪነት እንቅስቃሴዎች እየተስተዋሉ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዴሞክራሲ ሥርዓት ልምምድ የሰላምና አብሮነት ማጎልበቻ እንጂ የውጥረትና መገፋፋት ምክንያት ሊሆን አይገባም ብለዋል።

የጥላቻ ንግግሮችንና ሐሰተኛ የመረጃ ስርጭትን በመታገል ጠንካራ ኢትዮጵያን መገንባት ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።

''የሚሰራጩ መረጃዎችን በመመርመርም ትክክለኛውን በመለየትና አዝማሚያዎችን በሚገባ በመገንዘብ ጠቃሚ የሆኑትን ማጎልበት ያልተገቡትን ደግሞ ማስወገድ ያስፈልጋል'' ነው ያሉት።

የጥላቻ ንግግሮችንና ሐሰተኛ የመረጃ ስርጭቶችን ለመከላከልም የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና ማሳደግ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ጥናት የማዘጋጀት አቅሙን እንዲያሳድግ የሚያደርጉ መፍትሔ አመላካች ሀሳቦችን ማቅረብም የመንግስት ሌላኛው ተግባር ይሆናል ሲሉ አመላክተዋል።

የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ፤ የውይይት መድረኩ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የጥላቻና ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት መከላከል ደግሞ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን አንስተዋል።

በመድረኩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 1185/2012 ዓ.ም የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨት የተከለከለ እና በህግ የሚያስቀጣ መሆንኑ መደንገጉ ይታወቃል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም