ኢንተርፖል ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ባካሄደው ኦፕሬሽን 94 ሰዎችን አዳነ

3022

መስከረም 2/2011 ዓለም አቀፍ የፖሊስ ተቋም (ኢንተርፖል) ሱዳን ውስጥ 94 ሰዎችን ከህገወጥ የሠዎች አዘዋዋሪዎች መታደጉን አስታወቀ፡፡

ሲጂቲኤን ባወጣው ዘገባ እንዳመለከተው ኢንተርፖል ከታደጋቸው ሰዎች ውስጥ 85ቱ ህፃናት ሲሆኑ ከቻድ፣ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጎንጎ፣ከሱዳን፣ከደቡብ ሱዳን፣ከኤርትራና ከኒጀር የመጡ መሆኑ ታውቋል፡፡

እንደኢንተርፖል ገለፃ ሰዎቹን ከህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች መታደግ የተቻለው ለአራት ቀናት በተካሄደ ኦፕሬሽን ነው፡፡

“ሳውያን” የተሰኘው ኦፕሬሽን በካርቱም የኢንተርፖል ማእከልና በሱዳን ባለስልጣናት ትብብር የተከናወነ ነው፡፡

ኢንተርፖል ካስለቀቃቸው ሰዎች እድሜያቸው እስከ አስር ዓመት የሆኑ ህፃናት የነበሩ ሲሆን በህገወጥ የወርቅ ማዕድን ማውጫ በአደገኛ ሁኔታ ሲሰሩ የነበሩ መሆኑ ታውቋል፤በአደገኛ ኬሚካሎችም እንዲሰሩ ተገደዋል ብሏል ኢንተርፖል፡፡

የኢንተርፖል የፖሊስ አገልግሎቶች ዋና ዳይሬክተር ቲም  ሞሪስ እንዳሉት በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ታግተው የነበሩት ሰዎች የተለያየ ዜግነት ያላቸው መሆኑ የችግሩን ድንበር ተሻጋሪነትና ውስብስብነት ያሳያል፡፡

በመሆኑም ችግሩን ለመቅረፍ በፖሊስና በባለድርሻ አካላት የመረጃ ልውውጥ፣ ዓለም አቀፍ ትብብርና ጥሩ ልምዶችን መጋራት ያስፈልጋል ብለዋል ፡፡

ኦፕሬሽኑ በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪነት የተጠረጠሩ ሁለት ወንዶችንና 12 ሴቶችን በቁጥጥር ስር አውሏል፤20 ሺህ የአሜሪካን ዶላርም ማዳን ተችሏል፡፡

ኢንተርፖል ከህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ነጻ ያወጣቸው ሰዎች በሱዳን ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ዘገባው አመልክቷል፡፡