በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች የሴት ስራተኞችን የአመራርነት ሚና ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ውጤት እየታየበት ነው

125

ሰኔ 21/2014 /ኢዜአ/ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ የሴት ስራተኞችን አመራርነት ሚና ለማሳደግ በትግበራ ላይ ያለው ‘ስራዬ’ የተሰኘው መርሃ ግብር ውጤት እየታየበት መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የዓለም አቀፉ ሥራ ድርጅት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ‘ስራዬ’ በሚል ከግልና ከመንግስት የሶስትዮሽ አጋሮቹ ጋር በመተባበር በጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች አካታችና የመልካም ስራ ኢንዱስትሪን ማስፈን ላይ ያተኮረ ፕሮግራም እየተገበረ ይገኛል።

ፕሮጀክቱ የሰራተኞች መብት፣ ክፍያና ካሳን፣ እኩልነትና ውክልናን ማረጋገጥ፣ የመንግስት ተቋማትን ግልፅነትና ተጠያቂነት ማበረታታት እና ኢንደስትሪውን ምርታማነት ማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው።

በዚህም በተለይም ሴት የፋብሪካ ሰራተኞች በአቅም ግንባታ ረገድ በፕሮጀክት ትግበራ የተገኙ ውጤቶችን የሚገመግም የሁለት ቀናት የምክክር መድረክ ተጀምሯል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ፤ ሴቶች በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች ያላቸው ተሳትፎ በቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም በአመራር ሰጭነት ግን ሚናቸው ያነሰ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ከዓለም የስራ ድርጅት ጋር በመተባበር የሴቶች የአመራርነት ክህሎት ስልጠናዎች ሲሰጡ መቆየቱን አውስተው፤ በስልጠናው መሰረት ሴቶች በተለያዩ የአመራርነት ቦታዎች ውጤታማ እንደሆኑ ተናግረዋል።

ስልጠናው ሴቶቹን ቁጥራቸውን በሚመጥን ደረጃ ወደ አመራርነት ማምጣት የሴቶችን ተጠቃሚነት እና ምርታማነት ላይም የተሻለ ውጤት ለማምጣት ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል።

በቴክኒካል ስራዎች ሴቶች ያላቸው ብቃት በፋብሪካዎች ተመራጭ እንዳደረጋቸውም አስታውሰዋል።

በኮቪድ ወረርሽን ወቅት በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ ሴት ሰራተኞች ከስራ የመሰናበት ችግሮች ተደቅኖባቸው እንደነበርም አውስተዋል።

መንግስት ከረጂ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ሴቶች ለማህበራዊ ቀውስ ውስጥ እንዳይገቡ በርካታ ስራዎች ማከናወኑን ገልጸው ‘ስራዬ’ ፕሮግራምም ሴቶች አመራርነት ሚና እንዲኖራቸው ማስቻሉን ገልጸዋል።

መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የኢንዱስትሪ ሴት ሰራተኞች ወደ አመራርነት የማሳደግ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋገጠዋል።

ዓለም ስራ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ተወካይና የ’ስራዬ’ ፕሮግራም ኅላፊ ቅድስት ጫላ፤ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በትግበራ ላይ የሚገኘው ፕሮግራሙ መልከ ብዙ ውጤታማ ስራዎች ማከናወኑን ጠቅሰዋል።

በፕሮግራሙ ለሴት ሰራተኞች ምቹ የስራ ምህዳር በመፍጠር፣ የአመራርነት ብቃት ስልጠና በማመቻቸት፣ ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ሴቶችን በገንዘብ መደገፍ መቻሉን ተናግረዋል።

በኮቪድ 19 ወረርሽን ወቅት በ46 ፋብሪካዎች ውስጥ ለሚሰሩ ከ14 ሺህ ሰራተኞች ለማህበራዊ ቀውስ እንዳይዳረጉ የአምስት ወራት ደሞዝ መከፈሉን አስታውሰዋል።

የሴቶችን አመራርነት ብቃት ለማሳደግ ከ55 ሺህ በላይ ሰራተኞች ካቀፉ 49 ፋብሪካዎች ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከ100 በላይ ሰራተኞች የአመራርነት ስልጠና ወስደው 80 በመቶ የሚሆኑት በአመራርነት ቦታ ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል።

በመድረኩ ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን ውጤታማ የኢንዱስትሪ ሴት ሰራተኞች፣ አሰሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።