በባህርዳር ከተማ ቦምብ በማፈንዳት የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

99

ባህር ዳር ሰኔ 21/2014. በባህር ዳር ከተማ ትናንት ምሽት ህብረተሰቡን ለማሸበር አራት ቦታ ላይ ቦንብ በማፈንዳት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በፍንዳታው በሰውና ንብረት ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱም ተገልጿል።

በኮሚሽኑ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር መሰረት ደባልቄ በሰጡት መግለጫ ትናንት ምሽት አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ በባህር ዳር ከተማ በአራት ቦታዎች ቦንብ ፍንዳታ ተፈፅሟል።

ፖሊስ ባደረገው የተጠናከረ ክትትል ቦንቡን በማፈንዳት የተጠረጠሩ ስድስት ግለሰቦችን ከፍርድ ቤት ትዛዝ በማውጣት በቁጥጥር ስር አውሏል ብለዋል።

የተጠርጣሪዎቹ ቤት ሲፈተሽም ሶስት ብሬን፣ አንድ ስናይፐር፣ ሁለት ቦንብና 4 ሺህ 200 ተተኳሽ ጥይቶች እንዲሁም ለግንኙነት የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች መገኘታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ተግባር ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 14 ግለሰቦችም ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ለመፈጸም በዝግጅት ላይ እንዳሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስረድተዋል።

ግለሰቦቹ ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት በመፈጸም ጉዳት ለማድረስ የነደፉት የእቅድ ሰነድም አብሮ መያዙን ኮማንደር መሰረት አስታውቀዋል።

ተጠርጣሪዎቹ የቦንብ ፍንዳታውን የፈጸሙት በህዝቡ ላይ ሽብር ለመፍጠርና የክልሉን ሰላም ለማሳጣት ያለመ እንደሆነም ገልፀዋል።

የንጹሃን ዜጎችን ሞት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ክልሉን በመከፋፈል ለማተራመስ የሚሰሩ ኃይሎች ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኖ መገኘት ተቀባይነት የለውም ሲሉ ገልጸዋል።

በሌሎች አካባቢዎችም ሆነ በባህርዳር ከተማ  ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጸም ፖሊስ የተጠናከረ ስራ እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

ሰላም ወዳዱ የክልሉ ሀዝብ ለፖሊስ እያሳየ ያለውን ቀና ትብብር አጠናክሮ እንዲያስቀጥልም ጠይቀዋል።

የክልሉ መንግሥት ጥምር ኃይል እየወሰደ ያለው የህግ መስከበር ዘመቻ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ በማስከበር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም