የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሱዳን ምርኮኞችን በአደባባይ ገድሏል በሚል የሱዳን ጦር የሚነዛው መረጃ መሰረተቢስ ነው- መከላከያ ሚኒስቴር

201

ሰኔ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የምርኮኞችን አያያዝ ባልጠበቀ መንገድ ወታደሮቼን ገድሏል በሚል የሱዳን ጦር የሚነዛው መረጃ መሰረተ ቢስ መሆኑን የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ገለጸ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በቦታው እንዳልነበርና የኢትዮጵያን ግዛት ዘልቆ የገባው የሱዳን ኃይል ከአካባቢው ሚሊሻዎች ጋር መጋጨቱንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የመከላከያ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በሰጡት መግለጫ አሸባሪው ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በፈፀመበት ወቅት የሱዳን ሰራዊት የኢትዮጵያና የሱዳን ህዝብ ታሪካዊ ወዳጅነትን በማይመጥን መልኩ በኢትዮጵያ ግዛት ላይ ወረራ መፈጸሙን ጠቅሰዋል።

የሱዳን መከላከያ ኃይል በተለያየ ጊዜ ውስጣዊ ችግሮች ባጋጠሙ ቁጥር በኢትዮጵያ ላይ ትንኮሳዎችን ሲያደርግ መቆየቱንም ነው ያነሱት።

ከሰሞኑም የሱዳን ኃይል ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቆ በመግባት በአካባቢው በነበሩ የኢትዮጵያ ሚሊሻዎች ላይ ጥቃት ማድረሱንና ከሁለቱም ወገን ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

ይህም ሆኖ እያለ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በስፍራው ባልነበረበት ሁኔታ ምርኮኞችን ገደለ በሚል የሱዳን ጦር ክስ ማቅረቡ ተቀባይነት የሌለውና መሰረተ ቢስ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በቦታው አልነበረም ያሉት ኮሎኔል ጌትነት፤ ምርኮኞችን ቢይዝ እንኳን ሕግ አክባሪነት፣ ህዝባዊነትና ግዳጅ አፈፃፀም የሰራዊቱ መለያ ባህርያት ናቸው ነው ያሉት።

የሰራዊቱ ዲሲፕሊን በኮሪያና በኮንጎ ዘመቻዎች ጭምር የተመሰከረለት መሆኑን ጠቅሰው በሁለቱ ሱዳኖች የአብዬ ግዛት እንኳን በስነ ምግባሩ እንደተወደሰም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሰራዊት ከመንግስት ትዕዛዝ ሳይሰጠው እንደ ሽፍታ የሚንቀሳቀስ ቡድን ሳይሆን በጥብቅ የዕዝ ሰንሰለት የሚመራ ነው ብለዋል።

የደረሰውን ጥቃት በተመለከተ ማጣራት የሚፈልግ አካል ካለ ከሁለቱ አገራት መከላከያ ሰራዊት ተወካዮች የተውጣጣ ኮሚቴ ተዋቅሮ እንዲጣራ ለመተባበር የኢትዮጵያ ሰራዊት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም