የበዓሉ አከባበር ''የሁለቱን አገሮች ህዝቦች ፍላጎት ያሳካና የሰላምን ኃያልነት በተግባር ያንፀባረቀ ነው'' - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

58
አዲስ አበባ መስከረም 1/2011 አዲሱን ዓመት የኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር ሕዝቦችና የሰራዊት አባላት በጋራ ማክበራቸው ''የሁለቱን አገሮች ህዝቦች ፍላጎት ያሳካና የሰላምን ኃያልነት" በተግባር ያንፀባረቀ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር በቡሬና ዛላምበሳ ግንባር በመገኘት ከሁለቱ አገሮች ህዝቦችና መከላከያ ሰራዊቶች ጋር አዲስ ዓመትን አክብረዋል። በዚህ በዓል ላይ የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤልም ተገኝተዋል። ኩነቱ የሁለቱ አገሮች መከላከያ ሰራዊቶችና ህዝቦች በፍቅር የተቃቀፉበት እንዲሁም ሰንደቅ ዓላማቸው በጋራ የተውለበለበበት እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ገልጸዋል። አዲሱን ዓመት በጋራ ለማክበር ቃል በተገባው መሰረት በዓሉ የተከበረ ሲሆን፤ ለዓመታት ተቋርጦ የቆየው የየብስ ትራንስፖርት መጀመሩም ተበስሯል። ሁለቱ ህዝቦች በተገናኙበት ቅጽበት የተንጸባረቀው የደስታ ስሜት ሰላም ምን ያህል ዋጋ እንዳለው በተግባር የታየበት እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በዓሉን በጋራ ማክበር ያስፈለገውም ሰላምና ተስፋን በጋራ ሰንቆ ለመቀበል እንደሆነም ጠቁመዋል። የሁለቱ አገሮች ወታደሮች በድንበር ላይ በነበራቸው ቆይታ ብዙ ዋጋ መክፈላቸውን ያስታወሱት ዶክተር አብይ፤ የኢትዮጵያ ሰራዊት ከዛሬ ጀምሮ ወደካምፕ የሚሰባሰብ እንደሆነ ጠቁመዋል። በኤርትራም በኩል ተመሳሳይ ድርጊት የሚፈጸም እንደሆነም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሰራዊት ህብረተሰቡን በልማት የሚያግዝበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ገልጸው፤ ጦሩን ዘመናዊ ቁመና ለማላበስ የተለያዩ ስራዎች የሚከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል። የሁለቱ አገሮች መሪዎችና የሁለቱ አገሮች መከላከያ ሰራዊቶች አዲስ ዓመትን  በአንድነት ሆነው ሲያከብሩ ይህ የመጀመሪያው ነው። ይህ ግንኙነት በሁለቱ አገሮቹ መካከል በቅርቡ የተጀመረውና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የሰላም ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክር ነው የታመነበት። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በበዓሉ ላይ ከታደሙ በኋላ ዛሬ ከቀትር በኋላ አዲስ አበባ ተመልሰዋል። በወቅቱም ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ በሁለቱ አገሮች ህዝቦችና የሰራዊት አባላት መካከል የዘመን መለወጫን ማክበር ልዩ ክስተት እንደሆነ ነው ያመለከቱት። ''ክስተቱ የሁለቱን አገሮች ህዝቦች ፍላጎት ያሳካና የሰላምን ኃያልነት በተግባር ያንፀባረቀ መሆኑን መገንዘብ የተቻለበት ነው'' ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንደገለጹት፤ የሁለቱ አገሮች ህዝቦችና የሰራዊት አባላት በተገኙበት ዛሬ የተከበረው የዘመን መለወጫ በዓል የሰላምን ፋይዳ ከንግግር በላይ በተግባር ያረጋገጠ ነው። ክንዋኔው የሁለቱ አገሮች ሰንደቅ ዓላማዎች በጋራ መሳ ለመሳ የተውለበለበበት እጅግ ያማረ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውስተዋል። "ህጻናት፣ አረጋውያን፣ ወታደሮች በተፈጠረው አጋጣሚ ምን ያህል እንዳነቡ ስናይ፤ የሰው ልጅ በመጠላላት ለምን ወደ ጦርነት ይገባል የሚል ጥያቄ እንዲነሳ ያደርጋል" ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም