ለረጅም ጊዜ የተጓተተው የወጣቶችና ህፃናት ቲያትር ግንባታ ሊጠናቀቅ መሆኑ ተጠቆመ

99

ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለረጅም ጊዜ የተጓተተው የወጣቶችና ህፃናት ቲያትር ግንባታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአንድ አመት ውስጥ ባደረገው ርብብር ወደ መጠናቀቁ መቃረቡ ተጠቆመ።

የሃገር ፍቅር እድሳትም በተመሳሳይ ሊጠናቀቅ እንደሆነ ተገልጿል።የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ሕጻናትና ወጣቶች ቲያትር ግንባታንና የሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት የዕድሳትን ሥራዎች ጥቅል አፈጻጸም ገምግመዋል።

የቲያትር ቤቶቹ ፕሮጀክቶች ከትውልድ የስብዕና ግንባታ አስፈላጊነታቸው አኳያ በተያዘላቸው ፍጥነትና ጥራት እንዲጠናቀቁና ለታለመላቸው የትውልድ ግንባታ መዋል እስኪችሉ ድረስ አስተዳደሩ የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያደርግ ከንቲባዋ ተናግረዋል።

ለትውልድ ግንባታ ትኩረት ሰጥተን በሁሉም ረገድ ከተንቀሳቀሰን አገሩን አብዝቶ የሚወድ ዜጋ መፍጠር እንችላለን በማለት ገልጸው፤ ለተተኪው ትውልድ የሞራልና የስብዕና ግንባታ የሚጠቅሙ ሥራዎችን በመስራት አጠቃላይ ለውጡ እውን እንደሚደረግ ገልጸዋል።

አስቀድመን የትውልድ የስብዕና ግንባታ ላይ በሚገባው መልኩ ባለመሥራታችን ዛሬ እየገጠሙን ያሉ ጭካኔን የተሞላ ተግባራት በወገኑ ላይ ሲፈፀም እያየን በመሆኑ የትውልድ ግንባታ ላይ አበክረን ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር የጥበብ ተቋማት አስተዋጽኦቸው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፤ የጥበብ ስራዎችን በመደገፍ ከለውጡ ማግስት አንስቶ አስር አንፊ ቲያትር ቤቶችን የገነባን ሲሆን ጥረታችንን ለወደፊቱም አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል ማለታቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ አመልክቷል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤