ኢትዮ ቴሌኮም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ከተከላቸው ችግኞች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነው ጸድቋል

145

ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮ ቴሌኮም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ይፋ ከሆነበት 2011 ዓ.ም ጀምሮ ከተከላቸው 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ችግኞች 80 በመቶ የሚሆነው መጽደቁን አስታወቀ።

የተቋሙ ሰራተኞች ላለፉት ሶስት ዓመታት በአዲስ አበባ ሚሊኒዬምና እንጦጦ ፓርኮች በባለቤትነት ተረክበው የአረንጓዴ አሻራ በማኖር ያለሟቸው ስፍራዎች ተጎብኝተዋል።

የኢቲዮ ቴሌኮም ቺፍ ኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ መሳይ ውብሸት በአገር አቀፍ ደረጃ የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በተቋሙ ሰራተኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።

ለዚህም 91 ሚሊዬን ብር የሚጠጋ ወጪ መውጣቱን ገልጸው ይህ ሁሉ ሃብት የፈሰሰበትን የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ከግብ ማድረስና ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ችግኞቹን በሚገባ የሚንከባከቡ ሙያተኞችን በመቅጠርና አሰፈላጊውን ግብዓት በማሟላት የመንከባከብ ስራው በትኩረት ሲሰራ እንደነበር አንስተዋል።

በአዲስ አበባ በእንጦጦና በሚሊኒየም ፓርኮች ውስጥ ተቋሙ በባለቤትነት በተረከበው ስፍራ ላይ ያለማው የአረንጓዴ አሻራ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው በሚፈለገው መልኩ ጸድቋል ብለዋል።

የምዕራብ አዲስ አበባ ዞን ፋሲሊቲ ማናጀር አቶ ሙሉጌታ ካሳሁን በሚሊኒየም ፓርክ የተተከሉ ችግኞች አብዛኞቹ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ አይነቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም እየጠፉና እየተመናመኑ ያሉ አገር በቀል ዛፎችንና ለመድሃኒትነት የሚውሉ ተክሎች ይገኙበታል ብለዋል።

ችግኞቹን የማጽደቅና የማልማት ስራው በተጠናከረ መልኩ እንዲከናወን ለማድረግም በፓርኩ በተለያዩ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ሙያተኞችን በቋሚነት በመቅጠር እንዲንከባከቡ መደረጉን ጠቁመዋል።

በኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን አዲስ አበባ ዞን ፍሊት ማኔጅመንት ስራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል ተመስገን በበኩላቸው በእንጦጦ ፓርክ ተቋሙ ወደ 20ሺህ የሚጠጉ ችግኞችን በመትከል እየተንከባከበ መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የአካባቢው መሬት የባህርዛፍ ተክልን ብቻ የተላመደ በመሆኑ ሌሎች ችግኞችን በቀላሉ አያበቅልም።

በመሆኑም በተቋሙ የተተከሉ ችግኞች እንዲለሙ ለማድረግ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም አፈሩ ምቹና አብቃይ እንዲሆን ለማድረግ በትኩረት ሲሰራ እንደነበር አንስተዋል።

ነገር ግን በተደረገው የችግኝ እንክብካቤ ስራ የጽድቀት ምጣኔው እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመዋል።

በሚሊኒዬም ፓርክ የችግኝ አንክብካቤ ባለሙያው አቶ ከለለው ወልደአብ ችግኝን በመንከባከብ ለአገራቸውና ለማህበረሰባቸው ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ባሻገር በኢቲዮ ቴሌኮም የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው አብራርተዋል።

በዚህም በፓርኩ ከሚሰሩት የንብ ማነብ ስራ በተጨማሪ ችግኞችን በመንከባከብ የማጽደቅ ሃላፊነትን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም