በመተሐራ ከተማ ከ58 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቁ

79

አዳማ ፤ ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) በምስራቅ ሸዋ ዞን መተሐራ ከተማ ከ58 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት በቁ።

የውስጥ ለውስጥ የጠጠር መንገድ፣ የህዝብ መድሃኒት ቤት፣ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤትና የገበያ ማዕከላት ከተመረቁት የልማት ፕሮጄክቶች መካከል ይገኙበታል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ በወቅቱ፤  በዞኑ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 110 የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ዘንድሮ ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል።

በተለይ የዞኑ ህብረተሰብ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄ የሆኑት የመጠጥ ውሃ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ የገበያ ማዕከላትና የመንገድ ፕሮጀክቶች በበጀት ዓመቱ ትኩረት ያገኙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት እጦት የተቸገሩ ልጆችን ጨምሮ የመሰረተ ልማት ጥያቄ በተወሰነ ደረጃ መመለስ መቻሉን አቶ አባቡ ተናግረዋል።

አሁን ህዝቡ ከሚያነሳቸው የልማት ጥያቄዎች ውስጥ መድረስ የቻልነው የተወሰኑትን ነው፤ በአዲሱ የበጀት ዓመት ያደሩ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ አዳዲሶቹን በተያዘላቸው ጊዜ አጠናቀን ለአገልግሎት ለማብቃት እንሰራለን ነው ያሉት።

የመተሐራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደገፋ ዓለሙ፤ እየተገባደደ ባለው  የበጀት ዓመት የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች በ58 ሚሊዮን ብር ተገንብተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት ክፍት ተደርገዋል ብለዋል።

ለአገልግሎት የበቁትም የውስጥ ለውስጥ የጠጠር መንገድ፣ የህዝብ መድሃኒት ቤት፣ ቡኡራ ቦሩ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት፣ የገበያ ማዕከል፣ የመንገድ ዳር መብራትና የቢሮ ህንፃ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በተለይ በበጀት ዓመቱ ትኩረት የተሰጣቸው የህብረተሰቡ የረዥም ጊዜ ጥያቄ የነበሩ የልማት ፕሮጀክቶች መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም የእስካሁን ስራ መልካም መሆኑን አስረድተዋል።

ከመተሓራ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ሼህ ጀማል አህመድ በሰጡት አስተያየት፤  ከተማዋ ሰፊ የሆነ የመሰረተ ልማት ችግር እንደነበረባት ተናግረዋል።

በተለይ የመንገድ ዳር መብራት፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የህዝብ መድሃኒት ቤትና ቡኡራ ቦሩ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት በመሰራቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የረዥም ጊዜ የከተማዋ ህብረተሰብ ጥያቄ ምላሽ እያገኙ መሆኑን ነው  ያመለከቱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም