ቋሚ ኮሚቴው በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ ላይ ተጨማሪ ውይይት እንዲደረግ አቅጣጫ አስቀመጠ

83

ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ ላይ ተጨማሪ ውይይት እንዲደረግ አቅጣጫ አስቀመጠ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ ላይ ተወያይቷል።

ተቋማቱ ለአሰራር እንቅፋት ሆነውብናል ያሏቸውን የአዋጅ አንቀጾች በውይይቱ ላይ አቅርበዋል።የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በአዋጅ ቁጥር 1115/2011 ተቋሙ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሆኖ መቋቋሙን አስታውሰዋል።

ኢዜአ በኢትዮጵያና በህዝቦቿ ጥቅም ላይ ያተኮሩ ዜናና ዜና ነክ ዘገባዎች በማሰራጨት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ዋነኛ የዜና ምንጭ ለመሆን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ብሔራዊ መግባባት መፍጠርና አገራዊ ገጽታን መገንባት ከተቋቋመባቸው ተልእኮዎች ውስጥ ዋነኞቹ መሆናቸውን ገልጸዋል።እንደ ዴሞክራሲ ተቋም መረጃን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ መገናኛ ብዙሀን በማድረስ እንዲሁም ራሱን ለማደራጀት አዋጅ ቁጥር 1115/2011 የተሻለ አማራጭ መፍጠሩንም ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ተቋሙ ከሚሰበስበው ገቢ መጠቀም ባለመቻሉ፣ ተልዕኮውን ለመወጣት የሚያስችሉ ከፍተኛ ስራዎችን በሚፈለገው ጊዜና መጠን ለመፈፀም እንቅፋት እንደፈጠረበት ገልፀዋል።

ይህንኑ ለመፍታትም አዋጁ እንዲታይ ጠይቀዋል።እንዲሁም እየሰፉ የመጡ ስራዎችንና ተቋሙ በ2022 በአፍሪካ ቀዳሚ ለመሆን የያዘውን ራእይ በተሻለ አደረጃጀት ለመምራት የስራ አመራር ቦርዱ እንደ አስፈላጊነቱ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚዎችን መመደብ የሚያስችለው ስልጣንና ከተጠሪነት ጋር የተያያዙ በአዋጁ በግልጽ ያልተቀመጡ አንቀፆች እንዲሻሻሉም ጠይቀዋል።

ምክር ቤቱ በአዋጁ ላይ የተመለከቱትን ክፍተቶች በመመልከት ማስተካከያ እንዲደረግበት ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍስሀ ይታገሱ በበኩላቸው ተቋሙ በአገራዊ ሪፎርሙ ቅኝት እንዲጓዝ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመበት አዋጅ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ያሏቸውን ሀሳቦች አንስተዋል በዚህም ከግዥ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ከተቋሙ ስራዎች አንጻር በልዩ መታየት እንዳለበት አንስተዋል።

እንዲሁም ተቋሙ አመታዊ የመንግስት በጀት እንዲደረግለት እና ስልጣን እና ተግባሩ በግልጽ በአዋጁ መቀመጥ እንዳለበት ጠቁመዋል።

ከሚሰጠው አገልግሎት የቴሌቪዥን ግብር እየተገኘ ያለው ክፍያ ዝቅተኛ በመሆኑ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ይህንን ገቢ የሚያሳድግበት አሰራር በአዋጁ መካተት እንዳለበት ተናግረዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ጸገነት መንግስቱ ህጎች ሲወጡ ረዘም ላለ ጊዜ ማገልገል እንዳለባቸው ታሳቢ ተደርገው መዘጋጀት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በዛሬው መድረክ በሁለቱ ተቋማት ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ ላይ ጥንቃቄ የሚሹ ጉዳዮች መኖራቸውን አንስተው አዋጁን በድጋሚ ከባለሙያዎች ቡድን ጋር ማየት እንዲገባ ገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች መገናኛ ብዙሀን ዘመኑን የሚመጥን እና ብዝሀነትን ያቀፉ ስራዎች በስፋት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።የአዋጅ ማሻሻያዎቹ ከሌሎች ህጎች ጋር መጣረስ እንዳይፈጥሩ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በሚያሳውቀው መሰረት በቀጣይ የውይይት መድረክ እንደሚኖር በውይይቱ ማጠናቀቂያ ተገልጿል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም