ባለፈው የመኽር ወቅት በአሸባሪው ሕወሓት የታጣውን የሰብል ምርት ለማካካስ እየሰራን ነው- አርሶ አደሮች

107

ደሴ፤ ሰኔ 20/2014 (ኢዜአ) ''ባለፈው የመኽር ወቅት በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ምክንያት የታጣውን የሰብል ምርት በዘንድሮው መኸር እርሻ ለማካካስ እየሰራን ነው'' ሲሉ የደቡብ ወሎ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በአሸባሪው ህወሓት ወራራ ምክንያት የታጣውን ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት በዘንድሮ መኽር ወቅት ለማካከስ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተገልጿል።

በደቡብ ወሎ ዞን ወረኢሉ ወረዳ የ04 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መሀመድ ዘውዴ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፈው መኸር ወቅት በ2 ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት ጤፍ፣ ስንዴና አብሽ 50 ኩንታል ምርት ለማግኘት ሲሰሩ ነበር፡፡

ይሁን እንጅ ያለሙት ሰብል በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ምክንያት በአረም ተወርሶ፣ በእንሰሳት ተበልቶና ለምሽግ ተቆፍሮ ግማሽ ያህል ምርት እንኳ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

ዘንድሮ ያላቸውን 2 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም አልምተው ባለፈው ዓመት ያጡትን ምርት በማካካስ ከ60 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከሚፈልጉት የአፈር ማዳበሪያ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ማግኘታቸውን ጠቁመው ከግብርና ባለሙያው፣ ከአካባቢው አርሶ አደሮችና አጋር አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት የእርሻ ማሳቸውን ለዘር ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

በቃሉ ወረዳ የ033 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት  አርሶ  አደር አህመድ መሀመድ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት በአንድ ሄክታር መሬት ካለሙት ማሽላ፣ በቆሎና ጤፍ ስብሎች ከ30 ኩንታል በላይ ምርት ይጠብቁ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጅ በአካባቢው በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሰብላቸው ከመውደሙ ባለፈ ለምሽግ በመቆፈሩ  ምርቱ ከግማሽ በላይ መቀነሱን ጠቁመዋል።

በዘንድሮ የመኽር እርሻ ባለፈው አመት ያጡትን ምርት ለማካካስ አንድ ሄክታር መሬታቸውን አለስልሰው ለዘር ማዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።

 አስፈላጊውን የአፈር ማዳበሪያና የምርጥ ዘር ግብዓት በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

ባለፈው መኸር ወቀት 433 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በማልማት 12 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ ናቸው።

ይሁን እንጅ አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ወረራ የአርሶ አደሩ ማሳ በወቅቱ ባለመታረሙ፣ በእንሰሳት እንዲበላ በመደረጉና ምሽግ ተቆፍሮ የውጊያ ቦታ በመሆኑ በሰብሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።

በችግሩ ምክንያትም ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መታጣቱን ጠቁመው፤በዘንድሮው መኽር ወቅት ለማካከስ  እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለዚህም አርሶ አደሩ በእርሻ ትራክተር ጭምር ታግዞ ማሳውን አርሶ በኩታ ገጠም እንዲያለማና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ከ433 ሺህ 900 ሄክታር መሬት በላይ በተለያዩ የሰብል ዘር ለመሸፈን ታቅዶ  የእርሻ ስራ በማካሄድ የዘር ስራ መጀመሩን አመልክተዋል።

እየተሰራ ባለው ሥራ ከ12 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት መታቀዱን አመልክተዋል።

ምርታማነትን ለማሳደግም 484 ሺህ ኩንታል የአፈር ማደባሪያና 25 ሺህ ኩንታል  ምርጥ ዘር ለማቅረብ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ 294 ሺህ ኩንታል ሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያና 5 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም