የሃይማኖት ተቋማት ተከታዮቻቸውን በተግባር በሚገለጥ እምነት ማነጽ ይገባቸዋል

142

ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ)  የሃይማኖት ተቋማት ተከታዮቻቸውን በተግባር በሚገለጥ እምነት ማነጽ እንደሚገባቸው የእምነት አባቶች ተናገሩ፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖቶች ያሉ ሲሆን የእነዚህ ሃይማኖት ተከታዮች ለረጅም ዘመናት በመከባበርና በአብሮነት በመኖር ለዓለም ምሳሌ ሆነዋል።

የሃይማኖት ተቋማቱም ተከታዮቻቸውን በስነምግባር፣ በርህራሄ፣ በእዝነት፣ አንዱ ሌላውን በማክበር እንዲኖር እያስተማሩ ዛሬ ድረስ ዘልቀዋል።

ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ ግጭቶችና የፅንፈኝነት ተግባራት እየተስተዋሉ ነው።

እኒህን ችግሮች ለመፍታትም መንግስት ከሚወስዳቸው ህግ የማስከበር እርምጃዎች ባሻገር የሃይማኖት ተቋማቱ በትውልዱ ላይ ትክክለኛ የስነምግባር ቀረጻ ሊያካሂዱ እንደሚገባ በርካቶች ያነሳሉ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሃይማኖት አባቶች “ከመንፈስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ ሁሉ ከተግባር የተለየ እምነትም የሞተ ነው” ብለዋል።

በመሆኑም የየሃይማኖቱ ተከታዮች መጥፎ ነገሮችን እንዲያስወግዱና  በመልካም ስነምግባር እንዲኖሩ መስራት እንደሚገባ በማንሳት።

የሃይማኖት ተቋማት አብሮነትና አንድነትን በሚያጠናክሩና የህዝብን የጋራ እሴቶች በሚያስቀጥሉ ጉዳዮች ላይ አትኩረው በመስራት ትውልዱን የማነፅ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአብያተ ክርስቲያናት ተመራማሪ መጋቢ ሰላም ቀሲስ ሰለሞን ቶልቻ ትውልዱን በተግባር በሚገለጥ እምነት ማነጽ የሚቻለው ለህዝብ ምሳሌ የሚሆኑ የሃይማኖት አባቶችና መምህራን ሲበራከቱ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የሃይማኖት አባቶችና መምህራን ራሳቸውን የለወጡና ለሃይማኖታዊ አስተምህሮው ራሳቸውን የሰጡ መሆን አለባቸው ብለዋል።

የአልአቅሷ መስጊድ አስተዳዳሪ ሼህ አብዱልመናን ሁሴን፤ የሃይማኖት ተቋማት ራሳቸውን መፈተሸ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የእምነት አባቶችም ምእመኑን  በማስተማር፣ በመገሰጽ መልካሙን መንገድ በተግባር አርዓያ ሆነው ማሳየት እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የቅዱስ ፍራንሲስኮስ ቆሞስ አባ ፍስሀ ታፈሰ፤ የሃይማኖት መሪዎች የየሃይማኖቱን ተከታይ በእውነት እና በቅንነት በማስተማር ማነጽና ስነምግባራዊ ትምህርቱን በተግባር በመኖር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።  

በዚህም እያንዳንዱ ሰው ህሊናው ከክፉ ተግባራት እንዲቆጠብ ማድረግ ይቻላል ነው ያሉት።

የሃይማኖት አባቶቹ አክለውም አሁን ለሚታየው የሰላም እጦት መንስዔዎች “አለመደማመጥ፣ ራስ ወዳድ መሆንና ከእኔ ሌላ ማንም አይኑር” የሚሉ አስተሳሰቦች መሆናቸውን  ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ልዩነት ሳይገድበን በመደማመጥ፣ አንዱ ሌላውን በማክበርና እርስ በእርስ በመደጋገፍ  አሁን ካጋጠሙን ሀገራዊ ችግሮች መውጣት ይገባናል ብለዋል።

በየአካባቢው የሚስተዋሉ ግጭቶች እንዲወገዱም ተከታዮቻቸውን በተግባር በሚገለጥ ስነምግባር ማነፅና ሁሉም እንደየእምነቱ ለሀገሩ ሰላም መጸለይ ያስፈልጋል ነው ያሉት ፡፡