የታቦር ተራራ ልማት የከተማዋን የቱሪዝም እንቅስቃሴ የሚያሳድግ ነው-የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ

170

ሐዋሳ፤ ሰኔ 18/2014 (ኢዜአ) በሐዋሳ ሐይቅ ዳርቻ በሚገኘው የታቦር ተራራ በ200 ሚሊየን ብር ወጭ የሚከናወነው ልማት የሐዋሳ ከተማን የቱሪዝም እንቅስቃሴ የሚያሳድግ መሆኑን የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ አስታወቁ።

የታቦር ተራራን የማልማት ፕሮጀክት ከ20 በመቶ በላይ መከናወኑ ተመላክቷል።

በፕሮጀክቱ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ እንዳሉት  የሐዋሳ ከተማ ለቱሪዝም ኮንፍረንስ ያላት ተመራጭነት እየጨመረ መጥቷል፡፡

 የከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን የቱሪዝም እድገት ማጠናከር የሚያስችሉ ትላልቅ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን የማልማት ሥራ እያከናወነ  እንደሚገኝ አመላክተዋል።

 የከተማ አስተዳደሩ በመደበው በ200 ሚሊየን ብር ወጭ ግንባታው የተጀመረው የታቦር ተራራን የማልማት ፕሮጀክት አንዱ መሆኑን ጠቁመው፤ይህም የከተማዋን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በእጅጉ እንደሚያሳድግ ጠቁመዋል።

የታቦር ተራራ በሁሉም አቅጣጫ  ከተማዋን ሊያሳይ የሚችል መሆኑን አመልክተው፤ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት የሆነውን ተራራ ማልማት የሐዋሳ ገጽታን  በማጉላት ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ እንደ ሀገር የተያዘው የቱሪዝም ቦታዎችን የማልማት እንቅስቃሴ አካል እንደሆነ የተናገሩት ከንቲባው፤ ይህም  በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ሀገርንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር እንደ ሀገር በፍጥነት እየተከናወኑ ካሉ ፕሮጀክቶች በወሰደው ልምድ መነሻ ተራራውን የማልማት ስራው  በጥራትና በተያዘለት ጊዜ  እንዲጠናቀቅ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ተራራው በውስጡ የሚይዛቸው ፓርኮችና የተለያዩ መናፈሻዎች እንደሚኖሩት የገለጹት ከንቲባው፤ ፕሮጀክቱን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።፡

ተራራውን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በተያዘው እቅድ የተራራው ዙሪያ የአስፓልት መንገድ ሥራና የዙሪያው አጥር ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ አስቀድሞ ተጠናቋል ብለዋል።

ተራራውን ጨምሮ በከተማው እየተከናወነ ያለው የመሠረተ ልማት ግንባታ ስራ ከፍተኛ የስራ እድል እየፈጠረ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሐዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባና የማዘጋጃ ቤት ሃላፊው አቶ ሚልኪያስ ብትሬ ናቸው።

የተራራው ልማት ሲጠናቀቅ የከተማዋን ቱሪዝም ከማሳደግ ባለፈ በመዝናኛው ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶችና ለአካባቢው ነዋሪዎች  የሥራ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የተራራውን ግንባታ የሚያከናውነው ተቋራጭ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ጸጋዬ በበኩላቸው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በገቡት የስድስት ወር ውል መሰረት የመጀመሪያው ምዕራፍ ስራ ከተጀመረ  ከአንድ ወር በላይ ማስቆጠሩን ጠቁመዋል።

በእስካሁኑ ሂደት ከ20 ከመቶ በላይ ስራው መከናወኑን ገልጸው፤ በውሉ መሰረት ተራራውን የማስዋብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይ መወጣጫ ደረጃዎችን ጨምሮ ፋውንቴንና ሌሎች የፕሮጀክቱን ሥራዎች በማከናወን  ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ  እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በሐዋሳ ከተማ ታቦር ተራራ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ማርቆስ ኤሊያስ በበኩላቸው የሐዋሳ ከተማ እድገቷ ፈጣን መሆኑን ተናግረዋል።

ለከተማዋ እድገት የነዋሪዎቿና አመራሩ ድርሻቸው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ የታቦር ተራራን የማልማት ፕሮጀክት ከተማዋን የበለጠ ቱሪዝም ስበት ማዕከል እንድትሆን የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የተራራው ዳርቻ በአስፓልትና በእንሰት ቅርጽ በተሰሩ አጥሮች እንዲሰራ መደረጉ  የአካባቢው ውበት እንዲጨምር ማድረጉን ጠቁመዋል።

መንገዶቹ ለብስክሌትና ለእግረኛ ምቹ በመሆናቸው ብዙዎች ለመዝናናት የሚመርጡት ስፍራ መሆኑን ተናግረዋል።

የከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች የማልማት ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን የሐዋሳ ሐይቅን ለማልማት የሚያስችል ዲዛይን ተጠናቆ በመጪው ዓመት እንደሚጀመርም ታውቋል።