በጎንደር ከተማ አስተዳደር ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

117

ጎንደር ኢዜአ ሰኔ 19/2014 በጎንደር ከተማ አስተዳደር እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የከተማው ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ፡፡

የከተማውን የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር ምክክር ተካሂዷል።

የመምሪያው ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉቀን ብርሃኔ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከአምናው በ220 ሚሊዮን ብር ብልጫ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል።

ከተለያዩ የገቢ አርስቶች ዘንድሮ የተሰበሰበው ገቢ ከአምናው ብልጫ ቢኖረውም፤ የዓመቱን እቅድ ማሳካት ያልተቻለው በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረው የሰላም እጦት መሆኑንም ገልጸዋል።

የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩ አቡሃይ በበኩላቸው የንግዱ ማህብረሰብ ቀልጣፋና ተደራሽ የመንግሥት አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ የግብር ግዴታውን በወቅቱ እንዲወጣ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የተረጋጋ የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲጠናከርም የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ በኩል ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በከተማው በንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ አለማየሁ መኳንንት ''የንግዱ ማህብረሰብ ነግዶና አትርፎ ለከተማው ልማት የሚውል ግብር መክፈል እንዲችል የከተማውን ሰላምና ደህንነት ማጠናከር ይገባል'' ብለዋል።

የአንድ ከተማ ልማት የሚፋጠነው ከዜጎች በሚሰበሰብ ግብር በመሆኑ ግብር ከፋዮች ግዴታችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ሌላዋ ነጋዴ ወይዘሮ ዘርትሁን ተስፉ በበኩላቸው መንግስትና የንግዱ ማህብረሰብ ተቀራርቦ በመነጋገርና በመወያየት ረገድ ክፍተቶች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

የከተማው ግብር ሰብሳቢ ተቋም ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር የጀመረውን መልካም ግንኙነት በማጠናከር ቀልጣፋና ከሙስና የጸዳ አገልግሎት መስጠት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በምክክር መድረኩ ከስድስት ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ግብር ከፋይ ነጋዴዎችን ጨምሮ የከተማው አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

በጎንደር ከተማ አስተዳደር ከደረጃ  "ሀ" እስከ "ሐ" ከ24 ሺ 300 የሚበልጡ ግብር ከፋዮች እንዳሉ ከመምሪያ ኃላፊዋ ማብራሪያ ማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም