ኢትዮጵያ በሰላምና ልማት መስኮች ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር ትሰራለች- የአገር መከላከያ ሚኒስቴር

116

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በሰላም፣ ልማትና ሌሎችም የዲፕሎማሲ የትብብር መስኮች ከሁሉም ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር በመተማመን ላይ ተመስርታ የምትሰራ መሆኑን የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ገለጸ።

የመከላከያ ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቀማጭነታቸውን አዲስ አባባ ላደረጉ ወታደራዊ አታሼዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ተወካይ እና የመከላከያ የሜካናይዝድ ማስተባበሪያ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌ ሉላዊነት ባስተሳሰረው የዓለም ማህበረሰብ መደጋገፍና አብሮነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሁላችንም ጦር ሃይላችንን ለጦርነት የምናዘጋጀው ሰላምን በመጥላት ሳይሆን ሰላምን ለማረጋገጥ እንደሆነ ገልጸው፤ ይህም የአገርን ሉዓለዊነት እና ብሄራዊ ጥቅምን ለማስከበር እንደሆነ አንስተዋል።

ኢትዮጵያውያን ውስጣዊ ችግር ቢገጥማቸው እንኳን በታሪካቸው የውጭ ወራሪዎች ሲነሱ በጋራ ተነስተው ለአገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት እንደሚቆሙ በተደጋጋሚ እንዳሳዩ አስታውሰዋል።

በዓለም ላይ ጦርነት መነሻው ቀላል ቢሆንም ማብቂያውን ግን አዳጋች ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራሉ፤ ለሰላም፣ ለልማትና ትብብር ቀዳሚ ጉዳይ አድርገን ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

የዓለም ህዝብ ለሰላም፣ ለልማት እና ለፀረ-ድህነት ትግል ድምፁን ከፍ አድርጎ እያሰማ እንደሆነ ገልጸው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰላም ካልተረጋገጠ ልማት ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ  መረዳት አለበት ነው ያሉት።

በመሆኑም በሁሉም የዓለም ክፍል ሰላምና ደህንነትን ለማስፈን ሁላችንም በትብብር መስራት አለብን ብለዋል።

ኢትዮጵያ በመተማመን ላይ በመመስረት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰቡ ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳን ከሁሉም የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ጋር በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ በመተማመን ላይ የተመሰረቱ ስራዎችን መስራቷን እንደምትቀጥል ነው የገለጹት።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ መንግስት ወደ ትግራይ ክልል ያልተገደበ ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ ብዛት ያላቸው ሰብአዊ ድጋፍ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በየሳምንቱ ርዳታ እያጓጓዙ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

የተወሰኑ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት የተዛባ መረጃ በማሰራጨት የመንግስትን መልካም ተግባር ጥላሸት መቀባታቸው ትከክል አለመሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ከትግራይ በተጨማሪ በአማራና አፋር ክልሎች ያሉ ወገኖች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው መረዳት እንዳለበት ጠቅሰው፤ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም የኢትዮጵያን ህግ መሰረት ባደረገ አግባብ እንዲንቀሳቀሱ አሳስበዋል።

መንግስት ለሰላማዊ አማራጮች ቅድሚያ እንደሚሰጥ የተናገሩት አምባሳደር ዲና፤ በጦርነቱ የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ካሉ የሕግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም