በክልሉ 80 ሺህ ወጣቶች በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰማራሉ- ቢሮው

114

ሐረር ፤ሰኔ 18/2014 (ኢዜአ)፡ በሐረሪ ክልል በዘንድሮው ክረምት 80 ሺህ ወጣቶች የሚሳተፉበት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚካሄድ የክልሉ ሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ደሊላ ዩሱፍ አስታወቁ።

የቢሮው ኃላፊ ለኢዜአ እንደገለጹት የክልሉ  ወጣቶች   በዘንድሮው ክረምት በተለያዩ መስኮች  በከተማና በገጠር ወረዳዎች ለሁለት ወራት ለኅብረተሰቡ  የበጎ ፈቃድ  አገልግሎት ይሰጣሉ።

በአገልግሎቱ የሚሳተፉ ወጣቶች ቁጥርም  ከአምናው በ35 ሺህ  ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

 ወጣቶች የ100 የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች እንደሚያድሱ ጠቁመው፤በተጨማሪም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በመሳተፍ 1 ነጥብ 5 ችግኞች ይተክላሉ ብለዋል።

ደም ልገሳ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት፣የከተማ ጽዳት፣የከተማ ግብርናና ሌሎች የጎ አድራጎት ሥራዎች ወጣቶቹ የሚሰማሩባቸው  ዘርፎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ወጣቶቹ  በሚሰጡት አገልግሎት  ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ሥራ እንደሚያከናውኑ ወይዘሮ ደሊላ ተናግረዋል።

ወጣቶቹ  ባለፉት ዓመታት የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፤ በከተማ ፅዳት ፣የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ አርሶ አደሩን በእርሻው ሥራ በመደገፍ  በሰጡት አገልግሎት ውጤት መመዝገቡን ኃላፊዋ አመልክተዋል።

የሐረር ከተማ ነዋሪው ወጣት ሳላሀዲን እስክንድር  እንደገለጸው በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካማ ቤቶች እድሳትን ጨምሮ በተለያዩ ማህበራዊ እንቅስቃሴ እንደሚሳተፍ ተናግሯል።

 ከአሁን ቀደም በማህበራቸው  አቅመ ደካሞችን  ሲደግፍ እንደነበር ያስታወሰው ደግሞ በሐረር ከተማ  የህብረት ወጣቶች ማህበር አባል ኤርሚያስ  ጌታቸው ነው።

በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትም ማህበሩ አቅመ ደካሞችን ለማገዝ የሚያስችለውን  ሀብት በማሰባሰብ ላይ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን በሌሎች መስኮች እንደሚያጠናክሩም ገልጿል ፡፡

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወጣቶች በክረምት ወራት በቋሚነት ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠታቸው በመልካምነት የሚጠቀስ ባህል እየሆነ መጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም