የአሸባሪው ሸኔ የጥፋት ድርጊት የኦሮሞን ህዝብ የማይወክል አሳፋሪ ተግባር ነው – የባሌ ጎባ ነዋሪዎች

190

ጎባ፤ ሰኔ 17/2014(ኢዜአ)፡ -የአሸባሪውን ሸኔ የጥፋት ድርጊት የኦሮሞን ህዝብ የማይወክል አሳፋሪ የሆነ እኩይ ተግባር ነው ሲሉ በባሌ ዞን ጎባ ከተማ አስተያየተቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዎሪዎች ገለጹ።

መንግስት የአሸባሪ የሸኔ ቡድን የጥፋት ድርጊትን ለመግታት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉና  የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡም ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ሼህ ከድር በከር፤  ሸኔ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ንጹሃንን እየገደለ  ሀብት ንብረት በመዝረፍና በማውደም እኩይ ተግባሩን በህዝብ ላይ መፈጸሙን ኮንነዋል።

የሽብር ቡድኑን የጥፋት ድርጊት ለማስቆም  ብሎም ቡድኑን ለማጥፋት መንግስት እየወሰዳቸው ያለው እርምጃ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

“የቡድኑ ድርጊት ከኦሮሞ ባህልና ወግ ያፈነገጠ የጥፋት ድርጊት መሆኑን በመገንዘባችን መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ሀገራዊ አንድነት ለማጠናከር የሚያደርገው ጥረት እንዲሳካ የድርሻዬን እወጣለሁ” ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ አሰፋ ከተማ ናቸው፡፡

ኦሮሞ ትናንትም ዛሬም ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ተዋልዶና ተከባብሮ የኖረና  እየኖረ ያለ ህዝብ ነው፤  የማንንም ባህል የማይነካና በማንም ላይ ግፍ የማይፈፅም መሆኑ እሴቶቹ ይመሰክራሉ ብለዋል አቶ አሰፋ።

የባሌ ህዝብ አንድነቱን ይበልጥ በማጠናከር የሸኔን አሳፋሪና  እኩይ ድርጊት በማክሸፍ  የሰላም አምባሳደርነቱን በተግባር ማስመስከሩን መቀጠል እንዳለበት አመልክተው፤ እሳቸውም የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

አቶ ማህሙድ አብደላ በበኩላቸው፤ ሸኔ  ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ እየፈጸመ ያለውን የጥፋት ድርጊት በማውገዝ መንግስት የቡድኑን አፍራሽ ተግባር ለመግታት  እየወሰደ ያለውን እርምጃ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።  

ሸኔ የህዝቡን ሰላም በማወክ የክልሉን እድገት ለማቀጨጭ የሚሰራ ቡድን በመሆኑ የአካባቢያቸውን ሰላም ከመጠበቅ አልፎ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ቡድኑን ለማጥፋት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

 በተጀመረው ህግ ማስከበር ዘመቻ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን  መረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

አሸባሪው የሸኔ ቡድን በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚፈፅመው የጥፋት ድርጊት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠላት መሆኑን እንደሚያሳይ የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ መንግስትም የቡድኑን የጥፋት ተግባር  ለአንዴና ለመጨረሻ ለማስቆም እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመደገፍ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።