የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ይበልጥ ለማሳደግ የንግድ ትስስሩን ማጠናከር ያስፈልጋል

136

ሰኔ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ይበልጥ ለማሳደግ የንግድ ትስስሩን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማሀዲ ገለጹ።

በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በደቡብ ሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ባለሀብቶች የንግድ ስራቸውን እንዲያስፋፉ እና በትውልድ ሀገራቸው እንዲያሳድጉ የማገዝ ዓላማ ያለው ፎረም ትናንት በጁባ አካሂዷል።

በፎረሙ ላይ የጁባ ከተማ ከንቲባ ሚካኤል ላዱ አልሃጃቡና የደቡብ ሱዳን የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጸሀፊ ኦኮም ጄንስ ካርሎን ጨምሮ የደቡብ ሱዳን መንግስት ተወካዮች እንዲሁም በደቡብ ሱዳን በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈውበታል፡፡

በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማሀዲ እንዳሉት፤ የሁለቱ አገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጠንካራና የጠበቀ ታሪካዊ ዳራ ያለው ነው።

ይህንን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በሰላምና ደህንነት፣ በፖለቲካዊና በዲፕሎማሲ መስኮች ያለውን ትብብር የሚያጠናክር የንግድ ትስስር መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የጁባ ከተማ ከንቲባ ሚካኤል ላዱ አልሃጃቡ በበኩላቸው ደቡብ ሱዳንን ነጻ ለማውጣት በተደረገው ትግል ኢትዮጵያ ላበረከተችው አኩሪ አስተዋጽኦ የደቡብ ሱዳን መንግስት አድናቆት እንዳለው አስታውሰዋል።

"ወንድም እና እህቶቻችን ስለሆናችሁ በጁባ ንግዳችሁን ለመስራት የሚያስፈልጋችሁን ድጋፍ እንሰጣለን” ብለዋል።

የደቡብ ሱዳን የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጸሀፊ ኦኮም ጄንስ ካርሎ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን የንግድ ማህበረብ እንደ ማኑፋክቸሪንግ ባሉ ዘርፎች እንቅስቃሴያቸውን እንዲያሰፊ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ሚኒስቴሩ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን ኢኮኖሚና ንግድ ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም የኢትዮጵያውያኑ የንግድ እንቅስቃሴ ዙሪያ ጽሁፍ በፎረሙ ላይ ያቀረቡት አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ፤ በጁባ የሚገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቅርንጫፎች በደቡብ ሱዳን ለኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ስለሚሰጡት አገልግሎቶች ገለፃ አድርገዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን ንግድና ዘርፍ ማህበራት፣ ኢንዱስትሪ እና የግብርና ዘርፍ የስራ ሀላፊዎችም በህጋዊ የንግድ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ገለፃ አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያውያኑም በደቡብ የንግድ እንቅስቃሴያቸውን ለማስፋት እና ዘርፉ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትስስር እንዲያጠናክር የራሳቸውን ሚና ለመወጣት መስማማታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም